ኔታንያሁ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በፍልስጤም ይተገበራል ያሉት እቅድ ምን ይዟል?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ቁልፍ የሚባሉ ግቦች እስከሚጠናቀቁ ድረስ የእስራኤል ጦር መዋጋቱን ይቀጥላል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጸጥታ ካቢኔያቸው ባቀረቡት እቅዳቸው ውስጥ የእስራኤል ጦር በጋዛ በነጻነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ቢተገበር ያሉትን እቅድ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሀሙስ እለት ለጸጥታ ካቢኔያቸው ባቀረቡት በዚህ እቅዳቸው ውስጥ የእስራኤል ጦር በነጻነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ቁልፍ የሚባሉ ግቦች እስከሚጠናቀቁ ድረስ የእስራኤል ጦር መዋጋቱን ይቀጥላል።
- ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ጠ/ሚኒስትር ኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲያወጣ ጠየቀች
- የብራዚሉ ፕሬዝደንት የጋዛውን ጦርነት ናዚ ከፈጸመው ዘርማጥፋት ጋር ማነጻጸራቸው እስራኤልን ክፉኛ አስቆጣ
ሀማስን እና እስላማዊ ጅሀድን መደምሰስ እና በጋዛ ታግተው የሚገኙትን ሰዎች ማስለቀቅ ቁልፍ ከሚባሉት ግቦች ውስጥ መሆናቸውን ኔታንያሁ ጠቅሰዋል።
ኤኤፍፒ የእስራኤሉን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ጋዜጣን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የሲቪል ጉዳዮችን "ከሽብር ጋር ግንኙነት የሌላቸው" የአካባቢው ባለስልጣናት እንዲመሩት ማድረግ ቁልፍ ከሚባሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ እቅድ አንዱ ነው።
በእቅዱ መሰረት የትኛውንም አይነት የሽብር ጥቃት ለመከላከል የእስራኤል ጦር ላልተወሰነ ጊዜ በጋዛ ውስጥ በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ይደረጋል።
እስራኤል ቀደም ሲል በድንበር አካባቢ ከወታደራዊ ነጻ ቀጠና የመገንባት እቅዷንም እንደምትገፋበት በእቅዱ መካተቱ ተነገሯል።
ከዚህ በተጨማሪም እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እና በዌስትባንክ "የሽብርተኞች መጠናከር" እንዳይኖር እና ወደ እስራኤል የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመከላከል አጠቃላይ የዌስትባንክ ጸጥታን ለመቆጣጠር ማቀዷን ዘገባው ጠቅሷል።
ይህ እቅድ የግብጽ ጋዛ ድንበርንም ማውሳቱ ተገልጿል። እስራኤል ሽብርተኝነት እንዳያንሰራራ እና ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ሾልኮ እንዳይገባ ለማድረግ ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር የመዝጋት ፍላጎት አላት።
የሀማስን መሸነፍ የምትፈልገው አሜሪካ ግን በመሀመድ አባስ የሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር ቀስበቀስ ጋዛን ተረክቦ እንዲያስተዳድር ጥሪ አቅርባለች።
በቅርቡ ከግብጽ ጋር በምትዋሰነው የጋዛ ደቡባዊ ከተማ ራፋ ላይ ጥቃት በመሰንዘር አሉ ያለቻቸውን የሀማስ የመጨረሻ ምሽጎች እንደምትመታ እቅድ ማውጣቷን እስራኤል አስታውቃለች።
ይህን እቅድ ግብጽ እና የግጭቱ አደራዳሪ ሀገራት ተቃውመውታል።