እስራኤል ጋዛን ከግብጽ የሚያዋስነውን ድንበር ሙሉ በሙሉ ትቆጣጠራለች - ኔታንያሁ
“ጦርነቱ ከፍታው ላይ ደርሷል” ያሉት ኔታንያሁ፥ ደንበሩን መቆጣጠር የጋዛ ጦርነት ግባችን ስኬታማ ያደርጋል ሲሉ ተደምጠዋል
የኔታንያሁ ንግግር በ2005 ጋዛን ለቃ የወጣችው ቴል አቪቭ የቀደመ ውሳኔዋን መቀልበሷን አመላክቷል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸው ጋዛን ከግብጽ የሚያዋስነውን ድንበር ሙሉ በሙሉ እንደምትቆጣጠር ገልጸዋል።
“ጦርነቱ ከፍታው ላይ ደርሷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከግጭት ነጻ የሆነው የፊለደልፊ መተላለፊያ በእስራኤል እጅ መያዝ አለበት ብለዋል።
“መተላለፊያው መዘጋት አለበት፤ ከዚህ ውጭ ያሉ አማራጮች ሃማስን የመደምሰስ ዘመቻችን ስኬታማነት ችግር ውስጥ ይጥሉታል” ሲሉም ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ጠቁመዋል።
የእስራኤልን ጋዛን ከግብጽ የሚያዋስነውን ድንበር የመቆጣጠር ዝርዝር እቅድ ግን አላብራሩም።
የኔታንያሁ ንግግር በፈረንጆቹ 2005 ጋዛን ለቃ የወጣችው ቴል አቪቭ የቀደመ ውሳኔዋን መቀልበሷን አመላክቷል።
የእስራኤል ጦር ጋዛ የገባው ሃማስ ለመደምሰስ መሆኑን ቢገልጽም ጦርነቱ ሰርጡን ዳግም ሙሉ በሙሉ በእጁ ለማስገባት ያለመ ነው በሚል የሚነሱ ወቀሳዎችንም አጠናክሯል።
ኔታንያሁ 12 ሳምንታትን ያስቆጠረው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ለበርካት ወራት ሊቀጥል እንደሚችል መግለጻቸውም “ሃማስን የመደምሰስ ዘመቻው” በቀላሉ የሚሳካ እንዳልሆነ ማሳየቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል የሃማስ የጋዛ መሪው ያህያ ሲንዋር ምድር ቤት ጋር የተያያዘ ዋሻን ጨምሮ በጋዛ በርካታ የቡድኑን ዋሻዎች ማፈራረሷን መቀጠሏን እየገለጸች ነው።
ሃማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ በበኩላቸው በርካታ የእስራኤል ታንኮችን እና ተሽከርካሪዎችን ማቃጠላቸውንና ተዋጊዎቻቸውን በካን ዩኒስ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ሞርታሮችን በመተኮስ ጉዳት ማድረሳቸውን የሚያሳይ መግለጫ አውጥተዋል።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ በጦርነቱ ህይወታቸው የተቀጠፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 21 ሺህ 672 ደርሷል።
በጋዛው ጦርነት እስራኤል 172 ወታደሮቿ መገደላቸውን ይፋ አድርጋለች።