አሜሪካና አጋሮቿ በሄዝቦላህና እስራኤል መካከል ለ21 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቁ
ሀገራቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የጠየቁት በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት ነው
እስራኤል በትላንትናው እለት ብቻ በሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 72 ሰዎች ተገድለዋል
አሜሪካ እና አጋሮቿ በሊባኖስ እና እስራኤል መካከል የ21 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ አካላት ግጭቱን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር እንደሚያመቻች ተገልጿል፡፡
ሀገራቱ ከሊባኖስ በተጨማሪ የጋዛው ጦርነት ላይ ተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲደረግ እና ወደ ግጭት ማቆም ምክክሮች እንዲገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ከ79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም እንዲደረግ የጠየቁት ሀገራት አረብ ኤሜሬትስ፣ አውስትራሊያ፣ ሳኡዲአረብያ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ናቸው፡፡
በነጩ ቤተ መነግስት ይፋ በተደረገው የሀጋራቱ የጋራ አቋም መግለጫ ላይ በቀጠናው እያደገ የመጣው ሁሉን አቀፍ ጦርነት በአካባቢ ተጨማሪ የደህንነት ስጋት ማንገሱን ገልጾ በውጥረት ውስጥ የሚገኙ አካላት ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ ጠይቋል፡፡
ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በሊባኖስ መጠኑ ከፍ ያለ የአየር ጥቃት እየፈጸመች የምትገኝው እስራኤል በትላንትናው እለትም አጠናክራ በቀጠለችው ጥቃት 72 ሰዎች ሲገደሉ 223 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ሮይተርስ የሊባኖስ የጤና ሚንስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የእስራኤል ወታደራዊ አዛጅ በሊባኖስ የምድር ላይ ጥቃት ሊከፈት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ይህም ሲፈራ የነበረውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት የሚያስከትል ውሳኔ ሊሆን ስለሚችል ይህ ከመሆኑ በፊት ውጥረቱን ለማርገብ ነው አሜሪካ እና አጋሮቿ የተኩስ አቁም ጥሪውን ያቀረቡት፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ሀገራቸው ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን ለመመለክት ፈቃደኛ እንደሆነች ተናግረው በቀጠናው ሰላማዊ ድርድር እንዳይሳካ የምታበላሸው “የአካባቢው በጥባጭ” ኢራን ነች ሲሉ ከሰዋል፡፡
የኢራኑ አምባሳደር አባስ ርካቺ በበኩላቸው ኢራን በቀጠናው የሚገኝው ውጥረት ከዚህ የበለጠ እንዲሰፋ ባትፈልግም በሄዝቦላ እና እእራኤል መካከል ጦርነት ከተጀመረ ግን ቴሄራን ሄዝቦላህን እንድምትደግፍ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በነገው እለት በጠቅላላ ገፉባኤው ንግግር የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
ከጉባኤው ጎን ለጎንም አሜሪካ እና አራት አጋሮቿ ያቀረቡትን የሊባኖስ ተኩስ አቁም ስምምነት ጥሪ ከመሪዎቹ ጋር እንደሚመክሩበት ይጠበቃሉ፡፡
ቴልአቪቭ ከሰኞ አንስቶ በሊባኖስ የተለያዩ አካባቢዎች እየፈጸመችው በምትገኝው የአየር ጥቃት እስካሁን ከ550 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣብያዎች ውስጥይገኛሉ፡፡