እርምጃው የተወሰደው ከአሜሪካ አጋሮች ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር በመተባበር መሆኑን አሜሪካ አሳውቃለች
አሜሪካ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ በሰሜን ኮሪያ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ላይ አዲስ ማዕቀብ የጣሉት ፒዮንግያንግ በቅርቡ ላደረገችው የሚሳኤል ሙከራ ምላሽ ለመስጠት ነው።
ሐሙስ እለት ይፋ የሆነው የዋሽንግተን እርምጃ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የሦስት የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናትን ማንኛውንም ንብረት የሚያግድ ሲሆን ይህም በተገለለችው ሀገር ላይ ትልቅ ተምሳሌታዊ እርምጃ ነው ተብሏል።
አሜሪካ የግምጃ ቤት በተጨማሪም በጦር መሳሪያ ልማት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ናቸው ካላቸው ከጆን ኢልሆ፣ ዩጂን እና ኪም ሱ-ጊል ጋር ግብይት የሚፈጽም ማንኛውም ሰው ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ዝቷል።
በቅርቡ የተካሄደው የሰሜን ኮሪያ ሚሳይል ማስወንጨፍን ጨምሮ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራን "በአካባቢው እና በመላው አለም ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ይፈጥራል" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ማዕቀቡ "ለፒዮንግያንግ የመሳሪየ ልማት ፍጥነት፣ ስፋት እና የባለስቲክ ሚሳኤል ምጥቆች ምላሽ ለመስጠት ያለንን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት አጉልቶ ያሳያል" ብለዋል ብሊንከን።
ብሊንከን አክለውም እርምጃው የተወሰደው ከአሜሪካ አጋሮች ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር በመተባበር ነው ብለዋል።
ቶኪዮ እና ሴኡልም አዲሱን ማዕቀብ አስታውቀዋል።
ደቡብ ኮሪያ በማዕቀቧ አንድ የታይዋን እና የሲንጋፖር ዜጋን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦችን ኢላማ እንደምታደርግ ተናግራለች ሲል ቲአርቲ ዘግቧል።
ግለሰቦቹ ለሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር እና ሚሳይል ልማትና ማዕቀብ ለማምለጥ (ቀደም ሲል የነበረውን) አስተዋፅኦ አድርገዋል ሲል የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።
ሁሉም ግለሰቦች የአሜሪካ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ሚንስቴሩ አክሎም የደቡብ ኮሪያ አዲስ እገዳዎች "ከእነዚህ አካላት ጋር ሊደረጉ የሚችሉትን የግብይት ስጋቶች ለአገር ውስጥ እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ" ይዟል ብሏል።
“በሚስጥራዊው አገዛዝ የኒውክሌር እና የሚሳኤል ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ የተሳተፉ” ሰባት ተቋማትም መካተታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ አክሎ ገልጿል።
እርምጃው የፕሬዚዳንት ዩን ሱክ-ዮል አስተዳደር በግንቦት ወር ከጀመረ በኋላ ሴኡል በፒዮንግያንግ ላይ ማዕቀብ ስትጥል ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ጃፓን የራሷን ድርጊት ተከትሎ ለፒዮንግያንግ “ቀስቃሽ ድርጊቶች” ምላሽ በመስጠት የሶስት የሰሜን ኮሪያ ቡድኖች እና አንድ ግለሰብ ላይ ንብረት እንዳይንቀሳቀስ እግድ ጥላለች። .
ዋሽንግተን የሰሜን ኮሪያ የቅርብ አጋር የሆኑት ቻይና እና ሩሲያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጠንከር ያለ ማዕቀብ ለመጣል ያደረገችን ጥረት በመከልከላቸው ብስጭቷን ገልጻለች።