አሜሪካ፤ ሩሲያ እና ቻይና የሰሜን ኮሪያን የጦር ሰበቃ ይሁንታ እየሰጡ ነው ስትል ወቀሰች
ፒዮንግያንግ ሁሉንም የባላስቲክ ሚሳይል እና የኒውክሌር ሙከራዎችን የሚከለክለውን የተመድን ህግ እንድታከብር ጥሪ ቀርቦላታል
ቻይናና ሩሲያ በአሜሪካ የቀረበን የውግዘት መግለጫ አሻፈረኝ በማለት በፒዮንግያንግ ላይ የሚጣለውን አዲስ ጫና እና ማዕቀብ ተቃውመዋል
በሰሜን ኮሪያ ሰሞነኛ የሚሳይል ሙከራ ምክንያት አሜሪካ የፒዮንግያንግ አጋር ካለቻቸው ከሩሲያና ቻይና ጋር ተፋጣለች።
አሜሪካ እና አጋሮቿ የሰሜን ኮሪያን የቅርብ ጊዜ አህጉር አቋራጭ የባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራ አጥብቀው አውግዘዋል። የኒውክሌር እና የሚሳይል መርሃ-ግብሯን ለመገደብ እርምጃ እንዲወሰድ የጠየቁ ቢሆንም፤ ሩሲያ እና ቻይና በፒዮንግያንግ ላይ የሚጣለውን አዲስ ጫና እና ማዕቀብ ተቃውመዋል።
የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንደተናገሩት የባይደን አስተዳደር ሰሜን ኮሪያን “በህገ-ወጥ የባሊስቲክ ሚሳይል ሙከራና ሌሎች አደገኛ እንቅስቃሴዎቿ” የሚያወግዝ ፕሬዝዳንታዊ መግለጫ እንደሚያሰራጭ ተናግረዋል።
ፒዮንግያንግ የባላስቲክ ሚሳይል እና የኒውክሌር ሙከራዎችን የሚከለክለውን የተመድን እገዳ እንድታከብር ጥሪ ማቅረባቸውን አሶሸትድ ፕረስ ዘግቧል።
የፕሬዝዳንቱ መግለጫዎች በ15ቱ የም/ቤት አባላት ስምምነት እንዲፀድቅ የሚፈልግ ሲሆን፤ ሩሲያ እና ቻይና በሰጡት አስተያየት የሰሜን ኮሪያን ውግዘት መቃወማቸውን አመልክቷል ነው የተባለው።
በተመድ የሩሲያ ምክትል አምባሳደር አና ኢቭስቲኒቫ በአሁኑ ጊዜ "እየጨመረ ለመጣው ቀስቃሽ እና አደገኛ" ሁኔታ ምክንያቱ ግልጽ ነው ብለዋል። ይህም "ዋሽንግተን በፒዮንግያንግ ማዕቀብ በመተግበር በኃይል ትጥቅ እንድትፈታ የማስገደድ ፍላጎት" ነው ብለዋል።
በሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ-ደቡብ ኮሪያ የባህር ኃይል ልምምድን ጨምሮ በአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ወታደራዊ ልምምዶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ስጋት እንደፈጠረባት ባለፈው ሳምንት ተናግራለች።
ወታደራዊ እርምጃዎች እና አዳዲስ ማዕቀቦች በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ተጨማሪ ውዝግብ ስለሚፈጥሩ ያሰጋል ያሉት ኢቭስቲኒቫ፤ "ይህም ሰሜን ምስራቅ እስያ አካባቢ ወደማይታወቅ እና አደገኛ ቀውስ ሊመራ ይችላል ብለዋል።
የፀጥታው ም/ቤት እንቅፋት ከመሆን ይልቅ በኮሪያ መካከል የሚደረገውን ውይይትና ድርድርን መደገፍ ነው በማለትም የሩሲያን አቋም ገልጸዋል።
የቻይና የተመድ አምባሳደር ዣንግ ጁን በበኩላቸው “ሁኔታውን ለማቀዝቀዝ” ጥረቶች እና ውይይት እንዲደረጉ ጠይቀዋል።
አሜሪካ ተነሳሽነቱን በመውሰድ “ቅንነትን ታሳይ” ያሉት አምባሳደሩ ለሰሜን ኮሪያ ህጋዊ ስጋቶች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ወታደራዊ ልምምዶችን እንድታቆም እና ማዕቀቡ እንዲቃለል አሳስበዋል።
ዣንግ የፀጥታው ም/ቤት "በዚህ ጉዳይ ላይ ገንቢ ሚና መጫወት አለበት” ያሉም ሲሆን፤ ሁልጊዜ ሰሜን ኮሪያን ማውገዝ ወይም ጫና ማድረግ የለበትም ብለዋል።