ቻይና ለአለም ሰላም ከሰሜን ኮሪያ ጋር እሰራለሁ አለች
ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በላኩት ደብዳቤ ቤጂንግ አሁንም የፒዮንግያንግ ዋነኛ አጋር መሆኗን አረጋግጠዋል
አሜሪካ ግን ይህን ትብብር ደጋግማ ስትቃወመው ትደመጣለች
ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለአለም ሰላምና ደህንነት በጋራ መስራት እንደምትፈልግ አስታወቀች።
የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ የኮሚኒስት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለደረሳቸው የደስታ መግለጫ ምላሽ ልከዋል።
ሺ በመልዕክታቸው ሀገራቸው አሁንም ከሰሜን ኮሪያ ጋር በቀጠናው ብሎም በአለም ሰላምና ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደምትሰራ ማረጋገጣቸውን የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሊቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
አለም በየጊዜው ባልተጠበቁ ሁነቶች እየተለዋወጠች ቢሆንም ከፒዬንግያንግ ጋር ያለን ወዳጅነት አይለወጥም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
ሰሜን ኮሪያ ወደ ጎረቤቶቿ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ሚሳኤል ደጋግማ ባስወነጨፈች ማግስት ነው ቻይና የትብብር እጇ እንደማይታጠፍ ያስታወቀችው።
ፒዮንግያንግ አሜሪካ መድረስ የሚችል አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ከማስወንጨፏ ከቀናት በፊት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የቻይና አቻቸውን በኢንዶኔዥያ ባሊ ፊት ለፊት ሲያገኙ ቤጂንግ ወዳጇን አደብ እንደምታስገዛ አምናለሁ ብለው ነበር።
የሰሜን ኮሪያን ፀብ አጫሪነት በኢኮኖሚም ሆነ በፓለቲካው ቁልፍ አጋሯ የሆነችው ቻይና ታስቆም ዘንድ የተጠየቁት ጂምፒንግ የሰጡት ምላሽ ግን እንደሚፈልጉት አልሆነም።
ለኪም ጆንግ ኡን በላኩት ደብዳቤም ስለሚሳኤልና ኒዩክሌር ፓለቲካ ምንም አላሉም።
የህዳር 18ቱን አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ሙከራ ተከትሎ የፀጥታው ምክር ቤት በጠራው ስብሰባም ቻይና ከሌላኛዋ የፒዮንግያንግ አጋር ሩስያ ጋር የውግዘት ደብዳቤው ውስጥ ስማቸውን አላስገቡም ።
ይህ የሁለቱ የሰሜን ኮሪያ ወዳጆችን ተግባር አሜሪካ ስታጣጥለው ይደመጣል።
በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ እርምጃዎች እንዳይወሰዱ ቤጂንግና ሞስኮ በፀጥታው ምክርቤት ያላቸውን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያለአግባብ እየተጠቀሙበት መሆኑን በማንሳትም ትሞግታለች።
በበርካታ አለም አቀፍ የማዕቀብ እርምጃዎች እግር ተወርች ለታሰረችው ሰሜን ኮሪያ አሁንም ቻይና እና ሩስያ የማይቋረጥ አጋርነታቸውን እየገለፁ ነው።
ሰሜን ኮሪያ ከ90 በመቶ በላይ የንግድ ትስስሯን ከቻይና ጋር ማድረጓም ለዚህ እንደ ማሳያ ይነሳል።