አሜሪካ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊያን የነዋሪነት ፈቃድ እንዲያገኙ ፈቀደች
በዚህ ፈቃድ አማካኝነት ኢትዮጵያዊያኑ የ18 ወራት የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል
በአሜሪካ 272 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉም ተገልጿል
አሜሪካ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊያን የነዋሪነት ፈቃድ እንዲያገኙ ፈቀደች፡፡
በኢትዮጵያ በፌደራል መንግስት እና ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ከነበረው ህወሃት ጋር የተጀመረው ጦርነት ሁለት ዓመት ያለፈው ሲሆን ከአንድ ወር በፊት ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ከነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ወደ ግዛቷ የገቡ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው መመለስ ለማይችሉ ዜጎች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ለትምህርት፣ ለንግድ፣ ለጉብኝት እና በሌሎች ምክንያቶች ወደ አሜሪካ የገቡ ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ መቆየት እንደሚችሉ አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር አሌጃንድሮ ማዮርካስ እንዳሉት ሀገራቸው በኢትዮጵያ በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ምን እየተካሄደ እንዳለ እንረዳለን በዚህ ምክንያት ወደ ሀገራቸው መመለስ ላልፈለጉ ዜጎች የመኖሪያ ፈቃድ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ይህ የአሜሪካ ጊዜያዊ መኖሪያ ፈቃድ የሚሰጠው ግን ከፈረንጆቹ ጥቅምት 20/2022 በፊት ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አሜሪካ ለገቡ ኢትዮጵያዊያን ብቻ እንደሆነ ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ለኢትዮጵያዊያን በሰጠችው በዚህ እድል መሰረት 27 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከጦርነቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ባሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ወደ ሀገራቸው መመለስ ለማይፈልጉ ዜጎችም እድሉ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡
በዚህ የአሜሪካ እድል አማካኝነት ኢትዮጵያዊያኑ ለ18 ወራት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያገኛሉ የተባለ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ የመኖሪያ ፈቃዱ ሊራዘም ይችላልም ተብሏል፡፡
በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች 272 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩ የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል፡፡
ከሁለት ዓት በፊት የተጀመረውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሰላም ስምምነት ከአንድ ወር በፊት የተፈረመ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት የሰብዓዊ ድጋፎች እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን መጀመራቸውን የኢትዮጵያ መንግስት እየገለጸ ነው።