የደቡብ አፍሪካ ድርድር ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ መደበኛ ንግግር ነው
በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚደረገው ድርድር በዛሬው እለት በደቡብ አፍሪካ መካሄድ መጀመሩ ተገለፀ።
በዛሬ የተጀመረው የሰላም ድርድር እስከ ፊታችን እሁድ ቀጥሎ የሚካሄድ መሆኑንም የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለው የሰላም ድርድር ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከሁለት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ መደበኛ ንግግር ነው።
የፕሬዝዳንት ስሪል ራማፎሳ ቃል አቀባይ ቪንሴንት ማግዋይና፤ ደቡብ አፍሪካ ለሰላም ድርድሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።
ማግዌንያ አክለውም ደቡብ አፍሪካ ድርድሩ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ዘላቂ ሰላም ያመጣል የሚል እምነት እንዳት ገልጸዋል።
በአፍሪካ ህብረትአሸማጋይነት በሚካሄደው ድርድር ላይ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት በትናትናው እለት ተደራዳሪዎቻቸውን ወደ ደቡብ አፍሪካ መላካቸውን መግለጻውን ይታወሳል።
በሰላም ንግግሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ትናት ጠዋት ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራቱን የመንግሰት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፤ እነማ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደተጓዙ ግን የገለጸው ነገር የለም።
የህወሓት የተደራዳሪ ቡድን በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው ድርድር ላይ ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ መድረሳቸውን የህወሓት አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።
ፕሮፌሰር ክንድያ ህወሓትን ወክለው ወደ ደቡብ አፍሪካ የተላኩት አባለት ማንነታቸውን ግልጽ አላደረጉም፡፡ ነገርግን ቀደም ሲል ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ስር ለመደራደር ፍቃደኛ መሆኑን በገለጸበት መግለጫው ቡድኑ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን እና ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤን እንደሚያካትት መግለጹ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚስቴር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን የተደራዳሪውን ቡድን እንዲመሩ መሰየማቸውን መንግሰት ማስታወቁ ይታወሳል።