ፖለቲካ
በፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ የነበረው ድርድር ተራዘመ
ድርድሩ የፊታችን ቀዳሜ እና እሁድ እንዲካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት ነበር
ድርድሩ የተራዘመው ከሎጅስቲክስ ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል
በፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ የነበረው ድርድር ተራዘመ።
የአፍሪካ ህብረት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሆነ መናገሩ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት የፌደራል መንግስት እና ህወሓትን በደቡብ አፍሪካ እንዲደራደሩ ለሁለቱም ወገኖች ጥሪ አቅርቦም ነበር።
ሁለቱም ወገኖች ህብረቱ ያቀረበውን ጥሪ መቀበላቸውን እና በድርድሩ ላይ እንደሚሳተፉ መናገራቸው ይታወሳል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚካሄደው ይህ ድርድር ነገ እና ከነገ በስቲያ እንዲካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ይህ ድር ድር ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ድርድሩ ወደ መቼ እንደተራዘመ ያልተገለጸ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት ስለ ድርድሩ መራዘም እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ ነገ እና ከነገ በስቲያ በፕሪቶሪያ ሊካሄድ የነበረው ድርድር በሎጅስቲክስ ምክንያት ተራዝሟል።