አሜሪካ ሶስት የአልሻባብ መሪዎች ያሉበትን ቦታ ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደምትከፍል አስታወቀች
ሶስቱ የአልሻባብ መሪዎች በሶማሊያ እና ኬንያ የተፈጸሙ የሽብር ተልዕኮዎችን አቀነባብረዋል ተብሏል
ተፈላጊዎቹ አህመድ ድርዬ፣ ማሀድ ካራቲ እና ጀሀድ ሞስጣፋ እንደሆኑ ተገልጿል
አሜሪካ ሶስት የአልሻባብ መሪዎች ያሉበትን ቦታ ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደምትከፍል አስታወቀች።
በሶማሊያ እስላማዊ መንግስት የመመስረት ዓላማ አለኝ በሚል ከ20 ዓመት በፊት ትግል የጀመረው አልሻባብ የተሰኘው የሽብር ቡድን በምስራቅ አፍሪካ በርካታ አደጋዎችን አድርሷል።
አሜሪካ ይሄንን የሽብር ቡድን የሚዋጉ ሀገራትን ከሚደግፉ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን በሶማሊያ የአልሻባብ መሪዎች እና ታጣቂዎች አሉባቸው በሚባሉ ቦታዎች ላይ የአየር ላይ ጥቃቶችን በመሰንዘርም ላይ ትገኛለች።
አሁን ደግሞ አህመድ ድርዬ፣ ማሀድ ካራቲ እና ጀሀድ ሞስጣፋ የተሰኙ ሶስት የአልሻባብ መሪዎች ያሉበትን ለጠቆመኝ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደምትከፍል ተገልጿል።
ቪኦኤ በኬንያ የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ማርክ ዲላርድን ጠቅሶ እንደዘገበው ግለሰቦቹ ለአልሻባብ የገንዘብ እና ጦር መሳሪያ ድጋፎችን በማሰባሰብ እየደገፉ ነው ብለዋል።
አሜሪካ አልሻባብ በሶማሊያ እና በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ላይ እያደረሰ ያለውን የሽብር ጥቃት ለማስቆም ከአካባቢው ሀገራት ጋር እየሰራች መሆኗም ተገልጿል።
ያሉበትን ቦታ ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ከተተመነባቸው ከሶስቱ የአልሻባብ መሪዎች መካከል አንዱ አሜሪካዊ እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሀመድ የሚመራው የወቅቱ የሶማሊያ መንግሥት በአልሻባብ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት መክፈቱ ይታወሳል።
የሶማሊያ ፌደራል መንግስትን ለመደገፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ስር ለተሰማራው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጦራቸውን አዋጥተዋል።ተፈላጊዎቹ አህመድ ድርዬ፣ ማሀድ ካራቲ እና ጀሀድ ሞስጣፋ እንደሆኑ ተገልጿል