በአሜሪካ በ2024 ሙስሊም ጠል እንቅስቃሴዎች 70 በመቶ መጨመራቸው ተነገረ
በሙስሊሞች ላይ የሚፈጽሙ የተለያዩ ጥቃቶች እና ወንጀሎች ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ማሳየቱ ነው የተሰማው
በእስራኤል እና በሀማስ መካከል በጋዛ የሚደረገው ጦርነት ለጥቃቶቹ መጨመር ዋነኛ ምክንያት ነው
በአሜሪካ በፍልስጤማውያን እና በሌሎች የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የሚደርሱ የሙስሊም ጠል እንቅስቃሴዎች 70 በመቶ መጨመራቸው ተነግሯል፡፡
የእስራኤል እና ሃማስ ጦርነትን ተከትሎ ከአሜሪካ ባለፈ በመላው አለም የጸረ ሴማዊነት እና የሙስሊም ጠል ጥቃቶች ማሻቀባቸውን የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርት ያመላክታል፡፡
በአሜሪካ የሙስሊም መብት ተሟጋቾች ቡድን ካውንስል በበኩሉ በአሜሪካ ብቻ በ2024 ስድስት ወራት ውስጥ 4951 የተለያዩ በፍልስጤማውያን እና በሙስሊሞች ላይ የደረሱ ጥቃት ሪፖርቶች እንደደረሱት አስታውቋል፡፡
በርከት የሚሉት የጥላቻ ወንጀሎች ፣ጥቃት እና መገለሎች የሚደርሱት በስራ ቦታዎች ፣ በትምህርት ቤቶች ፣ በኢሜግሬሽን እና ጥገኝነት መጠየቂያ ቢሮዎች እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡
የሙስሊሞች መብት ተሟጋች ቡድኑ ባለፈው 2023 አመቱን በሙሉ በተመሳሳይ የደረሱ ጥቃቶች ቁጥር 8000 መሆናቸውን ሲገልጽ በዚህ አመት የተዘገበው የጥቃት መጠን በ70 በመቶ መጨመሩን የሚያመላክት ነው ብሏል፡፡
በዚህ አመት ከተከሰቱ አስደንጋጭ ጥቃቶች መካከል ጥቅምት ላይ በኢሊኖይ የ6 አመት ፍልስጤም አሜሪካዊ በስለት መወጋት፣ በቴክሳስ የተተኮሰባቸው 3 ተማሪዎች ፣በቬርሞንት የ3 አመቷን ህጻን በዋና ገንዳ ውስጥ አፍና ለመግደል ሙከራ ያደረገችው አሜሪካዊት እና ሌሎችም አደገኛ ጥቃቶች በሙስሊም እና ፍልስጤማውያን ላይ ተፈጽሟል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ዩኒቨርስቲዮች የጋዛውን ጦርነት ለመቃዎም በሚወጡ ፍልስጤማውያን ላይ ፖሊስ የሚወስደው እርምጃ ያልተመጣጠነ መሆኑን ካውንስሉ ቅሬታ አቅርቧል፡፡
ጥቅምት 7 ሃማስ የእስራኤልን ድንበር ተሻግሮ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል በኩል 1200 ሰዎች ሲገደሉ እስራኤል በጋዛ እያካሄደች በምትገኝው ጦርነት 40 ሺህ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 2.3 ሚሊየን የጋዛ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፋናቅለዋል፡፡