የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት፤ አሜሪካ እና አጋሮቿ ቻይናን ለመጨፍለቅና ለመቆጣጠር እየሰሩ ነው ብለዋል
አሜሪካ ለቻይና ያላትን “የተዛባ አመለካከት” እንድታስተካክል ተጠየቀች።
ቻይና፤ አሜሪካ ለቤጂንግ ያለት “የተዛባ አመለካከት” ካልለወጠች ግጭት ሊፈጠር የሚችልበት እድል ከፍተኛ መሆኑ ገለጸች፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ ከቻይና አመታዊ የፓርላማ ስብሰባ ጎንለ ጎን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከመቼውም ዘመናት በተለየ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው የቻይና-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠያቂዋ ዋሽንግተን መሆኗ ተናግረዋል፡፡
ዋሽንግተን በቤጂንግ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ ከምክንያታዊነት እና ትክክለኛ መንገድ ያፈነገጠ ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ "አሜሪካ ስለ ቻይና ያላት አመለካከት በጣም የተዛባ ነው"ም ብለዋል፡፡
አሜሪካ በፍትሃዊ ውድድር ከመሳተፍ ይልቅ ቻይናን በመጨፍለቅ እና በመቆጣጠር ላይ ትገኛለችም ነው ያሉት፤ በአሜሪካ የቀድሞ የቻይና አምባሳደርና የፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ታማኝ አማካሪ ኪን ጋንግ፡፡
በዓለም አቀፉ የጂኦ-ፖለቲካዊ ጉዳዮች ባላቸው ልዩነት በጊዜ ሂደት እየተቀዛቀዘ የመጣው የቻይና-አሜሪካ ግንኙነት አሁን ላይ በታይዋን እና በዩክሬን ጉዳይ እንዲሁም በቅርቡ በአሜሪካ ደቡብ ካሮላይና የባህር ዳርቻ የተመቱትን ፊኛዋች ምክንያት ይበልጥ እየተባባሰ መምጣቱ ይታወቃል፡፡
በተለይም “ሰላይ ናቸው” በተባሉትን የቻይና ፊናዋች ምክንያት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ቤጂንግ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ መሰረዛቸው ሀገራቱ ወዳልተፈለገ ግጭት እንዳይገቡ ስጋት ደቅኗል፡፡
ከፊኛዎቹ ጋር በተያያዘ በዋሽንግተን በኩል የሚቀርበው ክስ ውድቅ የያደረጉት የቻይናው ከፍተኛ ዲፕሎማት ኪን ፤ የፊኛዎቹ በአሜሪካ ሰማይ ላይ መታየት የአጋጣሚ ጉዳይ እንጅ ሌላ ሚስጥር የለውም ብለዋል፡፡
"አሜሪካ ፍሬን ካልያዘችና እና በተሳሳተ መንገድ መሄዷን ከቀጠለች ግጭት መፈጠሩ አይቀሬ ነው ፡፡ እናም የሚመጣውን አስከፊ መዘዝን የሚሸከመው ማን ነው?" ሲሉም ነው ማስጠንቀቂያ አዘል ጥያቄ ያቀረቡት፡፡
እንዲህ ያለው ውድድር የሁለቱ ህዝቦች መሰረታዊ ፍላጎቶች እና የሰው ልጅ የወደፊት እጣ ፈንታ ጭምር የሚወስን በመሆኑ “ጥንቃቄ የጎደለው ቁማር ነው" ሲሉም አሳስበዋል ሚኒስትሩ፡፡
በአሜሪካ የሚመሩት የምዕራባውያን ሀገራት ቻይናን ለመቆጣጠርና ለማፈን ባደረጉት ጥረት በቻይና እድገት ላይ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ፈተናዎችን አስከትሏል ማለታቸውም የሺንዋ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።