ቻይና ሩሲያና ዩክሬንን ላሸማግል ማለቷ በምዕራባዊያን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል
የዩክሬን ቀውስ ግጭቱን በመራዘም እና በማባባስ የማይታይ እጅ የሚመራው ይመስላል ሲሉ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኪን ጋንግ ተናገሩ።
- ለዩክሬን የጦር መሳሪያን በገፍ እየላኩ ያሉ ሀገራት እነማን ናቸው?
- ሩሲያ፤ ቻይና በዩክሬን ዙሪያ ያቀረበችውን ምክረ-ሃሳብ ለመቀበል"ጊዜው አሁን አይደለም" አለች
“የማይታየው እጅ” የዩክሬንን ቀውስ ለጂኦፖለቲካዊ አጀንዳዎች እየተጠቀመበት ነው በማለትም አክለዋል።
በቤጂንግ በተካሄደው ዓመታዊ የፓርላማ ስብሰባ ላይ የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፤ ቀውሱን ለመፍታት በተቻለ ፍጥነት ውይይት እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል።
"ግጭት፣ ማዕቀብ እና ጫና ችግሩን አይፈታውም። የሰላም ድርድር ሂደት በተቻለ ፍጥነት መጀመር አለበት። የሁሉም አካላት ህጋዊ የጸጥታ ስጋቶች መከበር አለባቸው" ሲሉ ኪን ጋንግ ተናግረዋል።
ቻይና በዩክሬን ጦርነት ላይ ያላትን አቋም በድጋሚ የተናገረችው በቤጂንግ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው አለመግባባት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ቻይና በግጭቱ ውስጥ ሩሲያን ለማውገዝ ፈቃደኛ ባለመሆኗ፤ አለመግባባቱን ላሸማግል ማለቷ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ኪን በተጨማሪም ቤጂንግ ለሁለቱም ወገኖች የጦር መሳሪያ አልሰጠችም ብለዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ቤጂንግ ለሩሲያ የመሳሪያ ዕርዳታን ልትልክ ነው በሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
"ቻይና የቀውሱ አካል አይደለችም እና ለሁለቱም ወገኖች የጦር መሳሪያ አላቀረበችም" ብለዋል።
ቻይና ማስጠንቀቂያውን መሰረተ ቢስም ብላዋለች።