አሜሪካ የደህንነት ስጋት ናቸው በሚል የዜድቲኢ እና ሁዋዌ መሳሪያዎችን ሽያጭ አገደች
የአሜሪካ ፌዴራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን እርምጃዎቹ ቀጣይ ናቸው ብሏል
አሜሪካ፤ ቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቿን በመጠቀም ትሰልለኛለች የሚል ስጋት አላት
አሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት አለብኝ በሚል የቻይና የሆኑትን አዳዲስ የዜድቲኢ የቴሌኮሙኒኬሽ እና የሁዋዌ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ሽያጭ አገዳለች፡፡
የአሜሪካ ፌዴራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን በትናንትናው እለት እንዳስታወቀው በቻይና የክትትል መሳሪያዎች ሰሪ ዳሁዋ ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ፣የቪዲዮ ክትትል ድርጅት ሃንግዙ ሂክቪዥን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን እና የቴሌኮም ኩባንያ ሃይቴራ ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የተሰሩ መሳሪያዎችን መሸጥ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን የሚከለክል የመጨረሻ ነው ያለው ህግ አጸድቋል፡፡
ውሳኔው ቤጂንግ የቻይናን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በመጠቀም አሜሪካውያንን ለመሰለል ትጠቀም ይሆናል በሚል ስጋት ዋሽንግተን በቻይና የቴክኖሎጂ ግዙፍ ድርጅቶች ላይ የወሰደችውን እርምጃ ነው ተብሎለታል፡፡
የአሜሪካ ፌዴራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን ኃለፊ ጄሲካ ሮዝንወርሴል "እነዚህ አዳዲስ ህጎች የአሜሪካን ህዝብ ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር በተያያዙ የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶች ለመጠበቅ የምንወስዳቸው ቀጣይ እርምጃዎች አካል ናቸው" ማለታቸው ሮይተረስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ይህንን ህግ ለማጸደቅ ተገደደችው በመጋቢት 2021 "ከቨርድ ሊስት" ተብሎ በሚጠራው የ 2019 የአሜሪካን የመገናኛ አውታሮች ለመጠበቅ በወጣው ህግ መሰረት አምስት የቻይና ኩባንያዎች ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት መሆናቸው መረጋገጡን ተከትሎ እንደሆነም ነው ሮዝንወርሴል የተናገሩት፡፡
የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ስጋት ናቸው ተብለው የተፈረጁት የቻይና ኩባኒያዎች ህዋዌ ፣ዜድቲኢ፣ሃይትራ ኮሚዩኒኬሽንስ ኮርፖሬሽን፣ ሂክቪዥን እና ዳሁዋ ናቸው፡፡
የአሜሪካ ውሳኔን ተከትሎ የሽያጭ እገዳ በተጣለባቸው ግዙፍ የቻይና ኩባኒያዎች በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡