አሜሪካ ለ24 ሰአታት ጥይት የሚሸጥ ማሽን አስተዋወቀች
ማሽኑ ሰዎች የሚፈልጉትን አይነት ጥይት በየትኛውም ሰአት ማግኝት እንዲችሉ እንደ ኤቲኤም አገልግሎት የሚሰጥ ነው
ጥይት የሚገዛው ሰው የሚፈልገውን መጠን እና አይነት በማስገባት ግብይቱን መፈጸም ይችላል
በአሜሪካ ስራ የጀመረው አዲስ የጥይት መሸጫ ማሽን እያነጋገረ ነው፡፡
ማሽኑ የጥይት እና ጦር መሳርያ ሱቆች ዝግ በሚሆኑበት ሰአት ተገልጋዮች ልክ እንደ ኤቲኤም ለ24 ሰአት አገልግሎት የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
ቬንዲንግ ማሽን በሚል የሚታወቀው ማሽን ከዚህ ቀደም የለስላስ መጠጦችን በመሸጥ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡
በኦክላሆማ ፣ ቴክሳስ እና አልባማ ግዛቶች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ማሽኑ የሰዎችን ፊት የሚመዘግብ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የተገጠመለት ሲሆን ግብይቱ ህጋዊ መሆኑን ለማረጋገጥ በቅድሚያ መታወቂያ እንደሚጠይቅም ታውቋል፡፡
የአሜሪካ ፌደራል ህግ ለጠመንጃዎች ጥይት ለመግዛት ከ18 አመት በላይ፣ ለሽጉጥ ደግሞ ከ21 አመት እድሜ በላይ ያላቸው ሰዎች ብቻ መግዛት እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡
ማሽኑን ተጠቅመው የጥይት ግብይት የሚፈጽሙ ሰዎች ያሻቸውን ያህል መጠን መግዛት የሚችሉ ሲሆን፤ በቅድሚያ የሚፈልጉትን አይነት ይመርጣሉ ቀጥሎም መጠኑን ካስገቡ በኋላ መታወቂያቸውን ስካን እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ። ከእዚም ክፍያውን በመፈጸም ያዘዙትን ያህል መጠን ጥይት ማሽኑ ያቀርባል ነው የተባለው፡፡
በአሁኑ ወቅት በሶስት የአሜሪካ ግዛቶች ላይ የተጀመረውን አገልግሎት ወደ ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶችም ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ሉዊዚያና እና ኮሎራዶ ግዛቶች የማሽን ገጠማው በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ተሰምቷል፡፡
በአሁኑ ሰአት በዘጠኝ ግዛቶች በ200 መድብሮች ማሽኑን ለማስገጠም ጥያቄ እንደቀረበላቸው የተናገሩት የማሽኑ አምራቾች ከደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ ለሚነሳባቸው ቅሬታ ሲመልሱ፤ ማሽኑ የሁሉንም ተጠቃሚዎች ፊት እና መታወቂያ መዝግቦ ስለሚይዝ አንድ ሰው በምን ያህል ቀናት ልዩነት ምን ያህል ጥይት ገዛ የሚለውን ለመከታተል ስለሚያስችል ከስጋት ነጻ ነው ብለዋል፡፡
የጅምላ ግድያ እና ተደጋጋሚ የጦር መሳርያ ጥቃት በሚፈጽመባት አሜሪካ የጦር መሳርያ ቁጥጥር ስራዎች አመርቂ ውጤት አልተመዘገበባቸውም፡፡
መሰል የጥይት መሸጫ ማሽኖች መበራከት ደግሞ የወንጀል ስርጭቱን ያሰፋዋል በሚል ነገሩን በስጋት የተመለከቱ ሰዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡
ይህ ማሽን አገልግሎት ላይ ከዋለባቸው ሶስት ግዛቶች መካከል አንዷ በሆነችው አልባማ በ2022 በጦር መሳሪያ በተፈጸም ጥቃት 1300 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በሌላኛዋ ግዛት ኦክላሆማ በዚሁ ምክንያት በየአመቱ 700 ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
እንደአሜሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ተቋም መረጃ ከሆነ በ2020 ከተፈጸሙ ግድያዎች 57 በመቶዎቹ በጦር መሳርያ የተደረጉ ናቸው፡፡