ሩሲያ በዩክሬን የማረከቻቸውን የምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች ለእይታ አቀረበች
ለሞስኮ ለእይታ ከቀረቡት የጦር መሳሪያዎች መካከል የአሜሪካ እና ጀርመን ታንኮች ይገኙበታል
ሩሲያ የጦር መሳሪያ ኤግዚቢሽኑን በኔቶ እና ዩክሬን ጥምረት የተከፈተባትን ጦርነት ድል እያደረገች መሆኑን ለዜጎቿ ለማሳየት ተጠቅማበታለች
በሩሲያ መዲና የሚገኘው የድል ፓርክ ከዩክሬን የተማረኩ የምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች ለእይታ ቀርበውበታል።
ሶቪየት ህብረት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚ ጀርመንን ማሸነፏን ለማውሳት የተከፈተው የድል ፓርክ ከትናንት ጀምሮ ሞስኮ በኬቭ ምዕራባውያንን ድል እያደረገች መሆኑን የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ማሳያ ሆኗል።
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ከማረካቸውና በፓርኩ ውስጥ ለእይታ ከቀረቡት ውስጥ የአሜሪካ አብራምስ እና የጀርመኑ ሊዮፓርድስ ታንኮች ይገኙበታል።
ጉዳት የደረሰበት የብሪታንያው “ሀስኪ” የተባለ ወታደራዊ ተሽከርካሪም በፓርኩ ውስጥ ለእይታ ቀርቧል።
በርካታ ጀርመን ሰራሽ የጦር መሳሪያዎችም “ታሪክ ራሱን እየደገመ ነው” ከሚል ጽሁፍ ጋር ተቀምጠዋል።
ቢቢሲ እንደዘገበው የሩሲያ ባለስልጣናት ከ30 በላይ ከዩክሬን የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን በሞስኮ የድል መታሰቢያ ፓርክ ለእይታ ያቀረቡት በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ይገመታል።
የመጀመሪያው ሞስኮ በምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ አይዞሽ የምትባለውን ኬቭ በመምታት ያስታጠቋትን መሳሪያ ጭምር መማረክ ችለናል የሚለውን ለማሳየት ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ሩሲያ በሁለተኛው የአለም ጦርነትም ሆነ በአሁኑ የዩክሬን ጦርነት ተገፍታ ወደ ጦርነት መግባቷንና ተጠቂ መሆኗን ለማመላከት ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
ሁለቱ ጦርነቶች ግን ለየቅል ናቸው፤ በፈረንጆቹ 1941 ጀርመን የያኔዋን ሶቪየት ህብረት ወራለች፤ በ2022 ደግሞ ዩክሬንን የወረረችው ሩሲያ ናት የሚለው ዘገባው፥ ያም ቢሆን ሩሲያውያን በድል መታሰቢያ ፓርኩ በመገኘት የሀገራቸው ጦር ያስመዘገበውን ድል እያደነቁ መሆኑን ያነሳል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት በመጀመሪያ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ስትል የገለጸችውን ጦርነት ለመጀመር የተገደደችው በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና የምዕራባውያን ያለቅጥ የመስፋፋት ፍላጎት እንደነበር መግለጿ ይታወሳል።
የተማረኩት የጦር መሳሪያዎችም ሞስኮ በኬቭ የምትዋጋው ኔቶ፣ አሜሪካን እና ሌሎች ምዕራባውያንን መሆኑን ለማሳየት ጠቅመዋታል።
በሞስኮ የድል መታሰቢያ ፓርክ “ድላችን አይቀሬ ነው” የሚል ጽሁፍ በትልቁ ያሰፈረችው ሩሲያ ከሰባት ቀናት በኋላ ሂትለር የተሸነፈበትን የድል ቀን ታከብራለች።