ኬንያ በካፒቶል ሂል ረብሻ ተሳትፏል በሚል የተጠረጠረውን ግለሰብ አሳልፋ ለአሜሪካ ሰጠች
ጥፋተኛነቱ ከተረጋገጠ ከ20 ለሚልቁ ዓመታት እስር ሊጠብቀው እንደሚችል ተነግሯል
በሁከቱ በነበረው ተሳትፎ በአሜሪካ ፖሊስ ሲፈለግ ነበር የተባለለት ግለሰቡ በትውልድ ሃገሩ ኬንያ ተሸሽጎ ነበር ተብሏል
ኬንያ ከሶስት ወር በፊት በአሜሪካ ነጩ ቤተመንግስት በተፈጠረ ሁከት የተጠረጠረውን ግለሰብ ለአሜሪካ አሳልፋ ሰጠች።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ስልጣናቸውን ለተመራጩ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ላለማስረከብ የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ እነደነበር ይታወሳል።
ከነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል በነጩ ቤተመንግስት “ካፒቶል” ህንጻ የተፈጸመው ረብሻ አንዱ ነው፡፡
ጆ ባይደን በምርጫው ማሸነፋቸውን ተከትሎ ሲመክሩ የነበሩ የአገሪቱ የምክር ቤት አባላትን ሲረብሹ የነበሩት ጽንፈኛ የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች ወደ ህንጻው በመግባት የተለያዩ ጥቃቶችን ፈጽመዋል፡፡
ከነዚህ ጽንፈኛ ጥቃት ፈጻሚዎች መካከልም አንዱ ትውልደ ኬንያዊው አሜሪካዊ አይሳክ ስተርጆን ነው፡፡ ስተርጆን ከረብሻው ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ፖሊስ እንደሚፈለግ ባወቀ ጊዜ ከአንድ ወር በፊት ወደ ኬንያ በመምጣት ራሱን ደብቆ ነበር።
ሆኖም የኬንያ መንግስት ሸሽጎ ሊያቆየው አልፈለገም፡፡ የ32 ዓመቱ ተጠርጣሪ ተላልፎ እንዲሰጥ በመወሰንም ከሁለት ቀናት በፊት ለአሜሪካ ፖሊሶች አሳልፎ ሰጥቶታል እንደ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ።
ተጠርጣሪው በአሜሪካ ኬኔዲ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሰ ጊዜ በኤፍቢአይ ፖሊሶች ቁጥጥር ስር ውሎ መታሰሩንም ዘገባው ጠቁሟል።
ስተርጆን በሞንታና ከተማ የራሱን ቢዝነስ በመምራት ላይ የነበረ ሲሆን የቀድሞው ፕሬዘዳንት ትራምፕ አፍቃሪ እንደሆነ ተገልጿል።
በጥቃቱ መሳተፉን ጠበቃው አስተባብሏል፡፡ ሆኖም ጥፋተኛነቱ በፍርድ ቤት ከተረጋገጠ ከ20 ዓመት በላይ እስር ሊጠብቀው እንደሚችል ተጠቁሟል።