አሜሪካ ትራምፕን ለመግደል አሲሯል ባለችው ኢራናዊ ላይ ክስ መሰረተች
ፋርሃድ ሻከሪ የተባለው ኢራናዊ ጥቅምት 7፣2024 ትራምፕን ለመግደል እቅድ መቀበሉን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ገልጿል
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ቃል አቀባይ ክሱ እስራኤል እና በውጭ የሚኖሩ የኢራን ተቃዋሚዎች "በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማወሳሰብ" የፈጠሩት ነው ብለዋል
አሜሪካ ትራምፕን ለመግደል አሲሯል ባለችው ኢራናዊ ላይ ክስ መሰረተች።
አሜሪካ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ተመራጩን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል አቀናብሮታል ከተባለው ሴራ ጋር በተያያዘ አንድ ኢራናዊ በትናንትናው እለት መክሰሷን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፋርሃድ ሻከሪ የተባለው ኢራናዊ ጥቅምት 7፣2024 ትራምፕን ለመግደል እቅድ መቀበሉን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ቃል አቀባይ እስማኤል በጋሂ በሰጡት መግለጫ ክሱ እስራኤል እና በውጭ የሚኖሩ የኢራን ተቃዋሚዎች "በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማወሳሰብ" የፈጠሩት ነው ብለዋል።
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴሩ የ51 አመቱ ሻከሪ በቴህራን የሚኖር የኢራኑ አብዮታዊ ዘብ ተባባሪ ነው ብሏል። ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ሻከሪ በህጻንነቱ ወደ አሜሪካ መሰደዱን እና በዝርፊያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ምክንያት 2008 ወደ የተባረረ ነው።
አቃቤ ህግ እንደገለፈው ከሆነ ሻካሪ አሁን ላይ በኢራን እንደሚኖር ይታመናል።
ሻካሪ በእስር ቤት ያገኛቸው ካርልሴ ሪቨራ እና ጆናታን ሎድሆልት የተባሉ ሁለት የኒው ዮርክ ነዋሪዎችም ሻካሪ የአሜሪካ ዜግነት ያለውን እና የኢራን መንግስት ግንባር ቀደም ተቃዋሚ የሆነን ሰው ለመግደል ባደረገው ሴራ ተባብረዋል ተብለው ተከሰዋል።
አቃቤ ህግ ኢላማ የተደረገው ማን እንደሆነ ግልጽ አላደረገም። ነገርግን የኢራን መንግስት አስገዳጅ የፊት መሸፈኛ ልብስ የምትቃወመው ጋዜጠኛ እና ማህበረሰብ አንቂ ማሲህ አሊነጃድ ልትሆን እንደሚችል ተገምቷል።
በ2021 እሷን ለማፈን አሲረዋል በሚል ተጠርጥረው አራት ኢራናውያን የተከሰሱ ሲሆን በ2022 ደግሞ ከቤቷ ውጭ ጠብመንጃ የያዘ ሰው በቁጥጥር ስር ውሏል።