አሜሪካ የመስከረም 11ዱን የሽብር ጥቃት 21ኛ ዓመት አስባ ዋለች
ዓለም የለወጠውና እስከ 3 ሺህ ሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡበት ጥቃት በ149 ደቂቃዎች ውስጥ የተፈጸመ ነበር
የ9/11ዱ የሽብር ጥቃት አሜሪካ በታሪኳ ከገጠሟት የሽብር ጥቃቶች ሁሉ የከፋው እንደሆነ ይነገራል
አሜሪካውያን በመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ምክንያት ያጧዋቸውን ወገኖቻቸውን የተመለከተ ዝክር በኒውዮርክ እያካሄዱ ነው፡፡
እንደፈረንጆቹ መስከረም 11 ቀን 2001 በኒው ዮርክ የዓለም የንግድ ማዕከል መንታ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች(ትዊን ታወርስ)፥ አርሊንግተን ቨርጂኒያ በሚገኘው የአሜሪካ የመከላከያ ሚንስቴር ህንጻ ፔንታገን እና በፔንሲልቬንያ ሻንክስቪል የተፈጸመው ጥቃት እስከ 3 ሺህ ሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸው ያጡበት አሳዛኝ ክስትት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም በአደጋው የሚወዷቸውን ያጡት አሜሪካውያን፤ በዌስት እና በቬሴ ጎዳናዎች ላይ የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት ሃያ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ እያከበሩ ይገኛሉ፡፡
በኒው ዮርክ ከተማ የጥቃቱ ፈጻሚዎች ባገቷቸው አውሮፕላኖች የወደሙት የዓለም የንግድ ማዕከል መንትያ ህንጻዎች አከባቢ እየተከበረ ባለው የመታሰቢያ ስነ-ስርአት ላይ፤ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስና ባለቤታቸው ጀነራል ዳግላስ ኤምሆፍ ተገኝተዋል፡፡
ስነ ስርዓቱ ላይ በርካታ ሰዎች የተገኙ ሲሆን በተለምዶ የተጎጂዎችን ስም ማንበብ እንዲሁም በማስታሰወስ አክብረውታል፡፡
የመስከረም 11ዱ ሙዚየሙ ለተጎጂ ቤተሰቦች ብቻ ክፍት መደረጉንም ነው የተገለጸው፡፡
ወደ ምሸት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ ፣ የዓለም የንግድ ማዕከል ህንጻዎች የሚያመለክቱ መንትያ ጨረሮች የከተማዋን ገጽታ እንደሚያበሩም ነው የኤንፒአር ዘገባ የሚያመላክተው፡፡
የመንትያ ህንጻዎቹ ቅርጽ የሚያሳዩት ጨረሮቹ በሰማይ ላይ እስከ አራት ማይል ድረስ ይደርሳሉም ነው የተባለው፡፡
የዛሬ 21 ዓመት በ149 ደቂቃዎች ውስጥ የተፈጸመው የ9/11ዱ የሽብር ጥቃት አሜሪካ በታሪኳ ከገጠሟት የሽብር ጥቃቶች ሁሉ የከፋው እንደሆነ ይነገራል፡፡
ጥቃቱ የደረሰው ከ21 ዓመታት በፊት ቢሆንም አሉታዊ ተጽዕኖው እስከ ዛሬ ድረስ መዝለቄንና በዚህም አሜሪካ ከዚህ ጥቃት በኋላ "ሽብር ላይ ጦርነት አውጃለሁ" ብላ አፍጋኒስታን እና ኢራቅን እንድትወር ሁሉ ምክንያት እንደሆናት ይነሳል፡፡
አሜሪካ ኦሳማ ቢል ላደንን ለመያዝ የአል ቃይዳ ምሽግ ናት የተባለችውን አፍጋኒስታን በ2001 እንዲሁም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ቡሽ “ጦርነቱ ከሽብር ጋር ነው” በሚል በ2003 ኢራቅን መውረሯ የሚታወስ ነው፡፡
አሁን የ9/11 የሽብር ጥቃት ከደረሰ ሃያ አንድ አመታት ተቆጥረዋል።
አሜሪካ በጥቃቱ ላይ ኦሳማ ቢን ላደን ቀጥሎ ትልቅ ሚና ነበረው ምትለውን የአልቃዒዳ መሪ አይመን አልዘዋሂሪ በቅርቡ በካቡል ባደረግቸው ኦፕሬሽን ብትገድልም፤ ጦሯ አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷና ታሊባን ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን መመለሱ፤ ወደ ሌላ ነውጥ እና ግራ መጋባት እንዳመራ ይነገራል፡፡