በኡጋንዳ የታሰሩት አሜሪካውያን ጥንዶች በሞት የሚያስቀጣ ክስ ተመሰረተባቸው
ጥንዶቹ በካምፓላ በማደጎ በተቀበሉት የ10 ዓመት ህጻን ላይ በፈጸሙት ከባድ ድብደባ ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት
በህጻናት ህገወጥ ዝውውር ተሳትፎ አድርገዋል በሚል የቀረበባቸው ተጨማሪ ክስም እሰከ ሞት የሚያደርስ ቅጣትን ያስከትልባቸዋል
በኡጋንዳ የታሰሩት አሜሪካውያን ጥንዶች የሞት ቅጣት የሚያስከትል ክስ ተመሰረተባቸው።
ኒኮላስ ስፔንሰር እና ባለቤቱ ማኔንዚ ሌግህ ስፔንሰር በፈረንጆቹ ታህሳስ 9 ቀን 2022 ነበር በካምፓላ በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ጥንዶቹ በህጻናት ማቆያ ላይ በሚገኝ የ10 ዓመት አካል ጉዳተኛ ህጻን ላይ በተደጋጋሚ ድብደባ እንደሚፈጽሙ ለፖሊስ ጥቆማ በመድረሱ ነው የተያዙት።
ፖሊስ በማዕከሉ ድንገተኛ ፍተሻ ሲያደርግ ህጻኑ በአሳዛኝ ሁኔታ ተጎሳቁሎ ተገኝቷል፤ ጣውላ ላይ ያለምንም ብርድ ልብስና ትራስ እንዲተኛ መገደዱን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስሎችንም መመልከት ችሏል።
- የኡጋንዳ ፕሬዝዳት ልጅ ጀነራል ሙሁዚ ኬኒሩጋባ ለአዲሷ የጣሊያን ጠ/ሚኒሰትር የጋብቻ ጥያቄ አቀረቡ
- የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ ኬንያዊያንን ይቅርታ ጠየቁ
ህጻኑ ጥንዶቹ በማደጎ ከተቀበሏቸው ሶስት ህጻናት አንዱ መሆኑንም የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ ያመላክታል።
የ32 አመት ጥንዶቹ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ጥብቅ ቁጥጥር ወደሚደረግበት ሉዚራ ማረሚያ ቤት የተወሰዱ ሲሆን፥ በከባድ ድብደባና በማደጎ የተቀበሉትን ህጻን በማሰቃየት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
አሜሪካውያኑ ጥንዶች ግን ክሱ መሰረተ ቢስ ነው ብለው ተከራክረዋል። ይህ ክስ እንዳለ ሆኖ በህጻናት ህገወጥ ንግድ ተሳትፎ አድርገዋል የሚል ተጨማሪ ክስም በትናንትናው እለት ቀርቦባቸዋል።
የጥንዶቹ ጠበቃ ግን ክሱ ምንም አይነት ተጨባጭ ማሰረጃ የማይቀርብበት ነው በሚል ውድቅ እንዳደረጉት ነው የኡጋንዳው ጋዜጣ ሞኒተር የዘገበው።
አቃቤ ህግ ግን ጥንዶቹ ህጻናትን በመመልመል ወደ ድብቅ ቦታ እየወሰዱ ጉልበታቸውን እንደሚበዘብዙና በህገወጥ የህጻናት ንግድ ላይ በስፋት እንደተሰማሩ ባቀረበው ክስ አመላክቷል።
ጥንዶቹ የቀረበባቸው የመጀመሪያው ክስ እስከ እድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን፥ በሁለተኛው ክስ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሞት ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
የኡጋንዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ያሳልፋል የተባለ ሲሆን፥ ስፔንሰርና ባለቤቱ መቼ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አልተገለጸም።
በካምፓላ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩት ነው ብሏል። የአሜሪካ መንግስት በ2020 በኡጋንዳ በመሰል ድርጊት የሚሳተፉ አካላት ላይ ማዕቀብ መጣሉ የሚታወስ ነው።