የአሜሪካ እዳ ለምን 31 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር ደረሰ?
የሀገሪቱ የእዳ ጫና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጅማሮ ከነበረበት በስድስት እጥፍ መጨመሩም ነው የተገለጸው
ዋሽንግተን በተለያዩ ሀገራት ጦርነትን ለመደገፍ የምታወጣው ወጪ ማደጉ ለእዳዋ መጨመር አንዱ ምክንያት ነው
የአሜሪካ የእዳ ጫና በቀጣዮቹ አስር አመታት በየአመቱ በ1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ዶላር እንደሚጨምር የሀገሪቱ ግምጃ ቤት አስታውቋል።
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛውን እዳ ያስመዘገበችው ሀገር ጠቅላላ እዳዋ 31 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር መድረሱንም ነው የገለጸው።
በሁለት አስርት አመታት ውስጥ 25 ትሪሊየን ዶላር እዳ ያስመዘገበችው ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ባለፈው ሳምንት የብድር ጣሪያዋን አልፋለች።
የሀገሪቱ የእዳ ጫና በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጅማሮ ከነበረበት በስድስት እጥፍ ስለመጨመሩ ነው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ያስታወቀው።
ሪፕብሊካኖች የብድር ጣሪያው እንዲያድግ ቢሞግቱም፥ የጆ ባይደን አስተዳደር የመንግስት ወጪዎችን መቀነስ ባለመፈለጉ እዳው ሊጨምር ችሏል ተብሏል።
ይሁን እንጂ ሁለቱም ፓርቲዎች ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ እየናረ ለመጣው እዳ ተጠያቂ ይደረጋሉ።
የሁለቱም ፓርቲዎች ፖለቲከኞች በተለያዩ ሀገራት ጦርነትን ለመደገፍ፣ ግብርን ለመቀነስ፣ የፌደራል መንግስት ወጪን ለማሳደግ እና ለአጣዳፊ ጉዳዮች ገንዘብ መበደርን አማራጭ አድርገዋል ነው የሚለው የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የእዳ ጫናውን በአሉታም በአዎንታም ይመለከቱታል።
31 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር የደረሰው እዳ የኢኮኖሚ ቀውስን የሚያመጣ ነው የሚሉት በአንድ ወገን፥ የፌደራል ተቋማት አቅምን ያጠናከረ እርምጃ በመሆኑ የእዳ ጣሪያውም ሊያድግ ይገባል የሚሉት በሌላ ወገን ይከራከራሉ።
ዋይትሃውስ እንደሚለው የዚህ አመት ብድር ለፌደራል ተቋማት የተያዘውን 6 ትሪሊየን ዶላር በጀት አንድ አምስተኛ የሚሸፍን ይሆናል።
አሜሪካ ከቦንድና ተያያዥ ምንጮች የምታገኘውን ብድር ለመመለስ ብትሞክር ካዝናዋ ባዶ ይሆናል የሚሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች፥ የእዳ ጣሪያው ከፍ እንዲል እየጠየቁ ነው።
ይሁን እንጂ ይዞት የሚመጣው የምጣኔ ሃብት ቀውስ የከፋ ስለመሆኑ የሚያነሱ ወገኖች እና ፖለቲከኞች ሙግትም በቀላሉ የሚታይ አልሆነም።
በርካቶች ግን አሜሪካ በተለያዩ ሀገራት ጦርነቶችን መደገፏን እስካላቆመች እና ከግብር የምትሰበስበውን ገንዘብ ካላሳደገች የእዳ ጣሪያዋ ከፍ ማለቱ አይቀሬ መሆኑን ይስማሙበታል።