ተመድ ለ54 ታዳጊ የዓለማችን ሀገራት የእዳ ስረዛ እንዲደረግላቸው ጠየቀ
የእዳ ስረዛው ለታዳጊ ሀገራቱ ካልተደረገ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አስከፊ ድህነት ይወርዳሉ ተብሏል
የእዳ ስረዛ እንዲደረግላቸው ከተጠየቁት መካከል 25ቱ የአፍሪካ ሀገራት ናቸው
ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለ54 ታዳጊ የዓለማችን ሀገራት የእዳ ስረዛ እንዲደረግላቸው ጠየቀ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሆነው የልማት ድርጅት ወይም ዪኤንዲፒ በመባል የሚጠራው ተቋም የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ለታዳጊ ሀገራት ባበደሯቸው ብድር ዙሪያ ሪፖርት አውጥቷል።
ድርጅቱ በሪፖርቱ እንዳመለከተው ለ54 የዓለማችን ታዳጊ ሀገራት የብድር ስረዛ እና ተጨማሪ የመክፈያ ጊዜ ወይም እፎይታ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
የብድር ስረዛ እንዲደረግላቸው ከተጠየቁት የዓለማችን ሀገራት መካከል 25ቱ የአፍሪካ ሀገራት እንደሆኑ ተቋሙ በድረገጹ ባወጣው ሪፖርት ላይ አስታውቋል።
ድርጅቱ አክሎም ለበለጸጉ ሀገራት እና ለአበዳሪ ተቋማት ትንሽ ነገር ቢያደርጉ ለታዳጊ ሀገራቱ ግን ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት አስታውቋል።
አበዳሪ ተቋማት እና ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት የብድር ስረዛ እና እፎይታ ካልሰጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አስከፊ ድህነት ሊወርዱ እንደሚችሉም ተገልጿል።
እንዲሁም አበዳሪ ተቋማት እና ሀገራት ብድሮቻቸውን ለድህነት ቅነሳ ስራዎች እንዲያውሉ ሊያበረታቱ ይገባል ሲልም ድርጅቱ አስታውቋል።
ኮሮና ቫይረስ፣ ግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ በርካታ የአለማችን ሀገራትን የግድ ቢሆንም ታዳጊ ሀገራት ግን የበለጠ ተጎጂ እንደሆኑም ተገልጿል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መከሰት በማገገም ላይ የነበረውን የዓለም ኢኮኖሚ ወደ ባሰ ጉዳት በመዳረግ ላይ እንደሆነ የገለጸው ድርጅቱ ታዳጊ ሀገራት በነዳጅ እና ምግብ ዋጋ መጨመር ምክንያት የበለጠ ተጎጂ እንደሆኑም ተገልጿል።