በኢትዮጵያ በህገወጥነት ይኖሩ የነበሩ 60 ሺህ የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ሰዎች መመዝገባቸው ተገለጸ
ሩሲያ ለኢትዮጵያ 162 ሚሊዮን ዶላር ብድር መሰረዝዋን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ያጎለብተዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ከሶቭየት ህብረት የተበደረቻቸውን ብድሮች መሰረዟን በይፋ አሳውቃለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከሶቭየት ህብረት ወይም አሁን ላይ ሩሲያ ተብላ ከምትጠራው ሀገር 162 ሚሊዮን ዶላር የተበደረችውን ገንዘብ ሰርዛለች ያሉት አምባሳደር መለስ በብድር መልክ ሊከፈል የነበረው ገንዘብ ለምን አገልግሎት መዋል እንዳለበትም ሁለቱ ሀገራት ተስማምተዋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለሩሲያ በብድር መልክ ልትከፍለው የነበረው 162 ሚሊዮን ዶላር ባልቻ ሆስፒታልን እና መልካ ዋከና የሀይል ማመንጫ ጣቢያ ለማዘመን እንዲውል መስማማታቸውም ተገልጿል።
ቃል አቀባዩ አቶምባሳደር መለስ በመግለጫቸው አክለውም፣ በኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ ይኖሩ የነበሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች ምዝገባ መጀመሩን እና እስካሁን 60 ሺህ ሰዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ምዝገባ የካናዳ፣ አሜሪካ፣ኮንጎ፣ ናይጀሪያ ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ኤርትራ ፣ሱዳን፣ቻይና፣ ቡሩንዲ ጋና፣ ህንድ፣ ባንግላዲሽ፣ ላይቤሪያ፣ ጣልያን እና የካሜሩን ዜግነት ያላቸው ህገወጥ ሰዎች መገኘታቸው ተገልጿል።
በዚህ ምዝገባ የተካተቱት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የቪዛ ጊዜያቸው የለፈበት፣ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ፣ የስደተኝነት ፈቃድ የሌላቸው እና ፈቃድ ለማግኝት በሂደት ላይ ያሉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ናቸው ተብሏል።
ዲፕሎማቶች፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ህጋዊ ቪዛ ያላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች በምዝገባው እንደማይካተቱም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ህገወጥ የውጭ ሀገራትን የመመዝገብ ስራው በአዲስ አበባ 21 ቦታዎች፣ የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፎች ሰበታ፣ ቡራዩ፣ ሆለታ፣ሱሉልታ፣ ለገጣፎ፣ ገላን እና ዱከም ከተሞች እየተመዘገቡ እንደሆነ ተገልጿል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ግብጽን ከጎበኙ በኋላ በካይሮ ስለ ህዳሴው ግድብ ተናገሩት ተብሎ የወጣውን መረጃ የሶማሊያ መንግሥት አቋም እንዳልሆነ ኢትዮጵያ ትረዳለችም ሲሉ አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
በግብፅ ብዙሃን መገናኛዎች የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ከግብጽ አቻቸው ጋር በጋራ ሆነው ተናገሩት ተብሎ የወጣው ዘገባ የአንድ ወገን አስተያየት ነው፣ በመሆኑም የሶማሊያ መንግስት በይፋ ስለ ህዳሴው ግድብ ያወጣው መግለጫ እንደሌለም ተገልጿል።