ሱዳን ለተመድ ያልከፈለችው 300 ሺ ዶላር ገደማ ውዝፍ እዳ አለባት ተባለ
ተመድ ልክ እንደ ሱዳን ሁሉ ውዝፍ እዳ አለባቸው ያላቸውን የ8 ሃገራት መብት አግዷል
እዳውን ተከትሎ ካርቱም በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔዎች የነበራትን ድምጽ የመስጠት መብት ማጣቷ ተነግሯል
ሱዳን የአባልነት መዋጮ አለመክፈሏን ተከትሎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔዎች የነበራትን ድምጽ ተነፈገች፡፡
ካርቱም የአባልነት መዋጯቸውን ሳይከፍሉ በመቅረታቸው በጠቅላላ ጉባዔው የነበራቸውን ድምጽ የመስጠት መብት ካጡ 8 ሃገራት መካከል ናት ተብሏል፡፡
193 የዓለም ሃገራትን በአባልነት ያቀፈው ጠቅላላ ጉባዔው የኮንጎ ሪፐብሊክን እና የጊኒን ድምጽ የመስጠት የአባልነት መብትም አግዷል፡፡
ኢራን፣ ቬንዙዌላ፣ አንቲጓና ባርቡዳ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ቫንዋቱም የአባልነት መብቱን ካጡ 8 ሃገራት መካከል ናቸው፡፡
ይህንንም የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዝዳንት አብዱላ ሻሂድ በጻፉት ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡
ጉቴሬዝ በደብዳቤው ሱዳን መብቷን መልሳ ለማግኘት 300 ሺ ዶላር ገደማ ገንዘብ መክፈል አለባት ብለዋል፡፡
ኢራን 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን፣ ቬንዙዌላ 39 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ መክፈል እንደሚጠበቅባቸውም ነው ዋና ጸሃፊው ያስታወቁት፡፡
ሁሉም አባል ሃገራት የአባልነት መዋጮን እንደሚከፍሉ የሚያትተው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ (ቻርተር) አንቀጽ 19 የአባል ሃገራቱ ያልተከፈለ ውዝፍ እዳ ቀደም ባሉት ሁለት ዓመታት ከከፈሉት ከበለጠ ድምጽ የመስጠት መብታቸውን እንደሚያጡ ያስቀምጣል፡፡
ሆኖም ይህ መክፈል የሚችሉበት ይዞታ ላይ ናቸው ወይስ አይደሉም ሲል የሃገራትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባል፡፡
በዚሁ አካሄድ መሰረትም ጠቅላላ ጉባዔው ውዝፍ እዳ ያለባቸው ሶማሊያ፣ ኮሞሮስ እና ሳኦቶሜውና ፕሪንስፔ መብታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡