ኢራን ቀጣናዊ ውጥረት እንዲፈጠር ባትፈልግም፣ እስራኤልን ግን "እቀጣለሁ" አለች
ቃል አቀባይ ይህን ያሉት የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ እስራኤል ሳታደርሰው አትቀርም በተባለው ጥቃት በኢራን ዋና ከተማ መገደሉን ተከትሎ ነው
የእስራኤል ባለስልጣናት እስካሁን ለሀኒየህ ለግድያ ኃላፊነት አልወሰዱም
ኢራን ቀጣናዊ ውጥረት እንዲፈጠር ባትፈልግም፣ እስራኤልን ግን "እቀጣለሁ" አለች።
ኢራን ቀጣናዊ ውጥረቱን የማባባስ ፍላጎት ባይኖራትም፣ ተጨማሪ አለመረጋጋትን ለማስቀረት እስራኤልን መቅጣት ያስፈልጋል ብለው እንደሚያምኑ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ቃል አቀባይ ይህን ያሉት የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ እስራኤል ሳታደርሰው አትቀርም በተባለው ጥቃት በኢራን ዋና ከተማ መገደሉን ተከትሎ ነው።
"ኢራን በቀጣናው መረጋጋት እንዲፈጠር ትፈልጋለች፤ ነገርገን ይህ የሚሳካው ተንኳሹን በመቅጣት እና ጽዮናዊው አገዛዝ ጥቃት ፈጸም እንዳይችል ማድረግ ሲቻል ነው" ያሉት ቃል አቀባዩ ናሰር ከናኒ ኢራን የአጸፋ ምላሽ መስጠቷ አይቀሬ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
አለምአቀፉ ማህበረሰብ በቀጣናው መረጋጋት ማምጣት ስላልቻለ በተንኳሹ ላይ የሚደረገውን ቅጣት መደገፍ አለበት ያሉት ካናኒ አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል። የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቴህራን የሚገኙትን አምባሳደር እና የተልእኮ ኃላፊ ከተጠባባቂው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ባግሪ ካኒ ጋር ተሰብስበው የኢራን እርምጃ አይቀሬነት ተነግሯቸዋል።
ከናኒ እንዳሉት ኦርጋናዜሽን ኦፍ እስላሚክ ኮኦፐሬሽን በሀኒየህ ግድያ ዙሪያ ውይይት እንዲያደረግ በኢራን ጥያቄ መሰረት በመጭው ረብዕ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሂዳል።
ኢራን እና አጋሮቿ ሀማስ እና ሄዝቦላን ጨምሮ በሀኒየህ ላይ ግድያ የፈጸመችው እስራኤል ነች የሚል ክስ እያሰሙ ናቸው።
ይህ ግድያ 11ኛ ወሩን ያስቆጠረው የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በሀማስ መሪዎች ላይ ከተፈሙት ግድያዎች ውስጥ አንዱ ነው።
የእስራኤል ባለስልጣናት እስካሁን ለግድያው ኃላፊነት አልወሰዱም። የኢራኑ አብዮታዊ ዘብ ጠባቂ ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት ሆሴን ሳላሚ በትናንትናው እለት "ጊዜው ሲደርስ እስራኤል ቅጣቷን ትቀበላለች" ሲሉ ዝተዋል።