አሜሪካ እስራኤልን ለማገዝ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ተጨማሪ ክፍለ ጦር ልታሰማራ ነው
ፔንታጎን በቀጠናው እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ ግዙፍ የውጊያ መርከቦችን ወደ አካባቢው አሰጠግቷል
ዋሽንግተን ለቴልአቪቭ ተጨማሪ የጦር መሳርያ ድጋፍ እንደምታደርግም አስታውቃለች
አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ተባብሶ የቀጠለውን ውጥረት ተከትሎ እራኤልን ለማገዝ ተጨማሪ ክፍለ ጦር ወደ ቀጠናው እንደምታሰመራ አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ የመከላከያ መስርያ ቤት ፔንታጎን ግዙፍ የውግያ መርከቦችን ወደ ቀጠናው ያስጠጋ ሲሆን በቅርቡ ለእስራኤል ተጨማሪ የጦር መሳርያ ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብቷል፡፡
የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ መሪ እስማኤል ሀኒየህ በኢራን ዋና ከተማ ተሄራን በሚሳኤል ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የጦርነት ስጋት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በኢራን እና በእስራኤል መካከል እያደገ የመጣው ውጥረት ወደለየለት ቀጠናዊ ግጭት እንዳያመራ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ከሀማሱ መሪ ግድያ ጋር በተያያዘ እስራኤል እስካሁን በይፋ ሀላፊነቱን ባትወስድም ቴሄራን እና ሌሎች የሀማስ ደጋፊዎች ቴልአቪቭ እጇ እንዳለበት በእርገጥኝነት በመናገር የከፋ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ዝተዋል፡፡
ሀኒየህ በተገደሉበት እለት በሰአታት ውስጥ የሂዝቦላን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ መግደሏን ያስታወቀችው እስራኤል ከኢራን እና ከሂዝቦላ የተቀናጀ ጥቃት ሊከተላት እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በኢራን እና እስራኤል መካከል ቆየት ያለ በጥላትነት የመተያየት ስሜት ቢኖርም የጋዛ ጦርነት መጀመር ፣ ቀጥሎም በሶርያ የኢራን ኢምባሲ ቅጥር ውስጥ እስራኤል የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ኢራን በቴልአቪቭ ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል፡፡
ፔንታጎን በአሁኑ ወቅት በቀጠናው ሁለት ግዙፍ የውግያ መረከቦችን አሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህ ውጭ ተጨማሪ ክፍለጦሮችን የያዙ መርከቦችን ወደ ስፍራው እንዲሰማሩ አዟል፡፡
ከነዚህ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከቦች ባለፈም በምድር ላይ የሚተከል የሚሳኤል መከላከያ ጥቅም ላይ ለመዋል ዝግጅት መደረጉ ነው የተሰማው፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን ውጥረቱ ከሚገኝበት ሁኔታ ጋር በተያያዘ የጦሩ አሰፋፈር ቅርጽ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ በሚችልበት ሁኔታ ሊቀያየር እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
በወታደራዊ እቅዱ ዙርያ ከእስራኤሉ አቻቸው ዮቭ ጋለንት ጋር በጉዳዩ ዙርያ እንደመከሩም ፔንታጎን አስታውቋል፡፡
ሁለቱ አካላት ተቀያያሪውን የቀጠናውን ሁኔታ በመመለክት የጋራ እቅዶችን ለማውጣት እና ለመተግበርም መስማማታቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡
ከሀማስ የፖለቲካ ቢሮ መሪ ግድያ ጋር በተያያዘ አሜሪካ እጇ እንደሌለበት ብታሳውቅም ለኢራን አልተዋጠላትም። የቴሄራን የስለላ ቢሮ ዛሬ ባወጣው መረጃ ዋሽግተን ጥቃቱ እንደሚፈጽም ታውቅ ነበር ብሏል፡፡
ኢራን እና ሂዝቦላ በእስራኤል ላይ ይፈጽሙታል ተብሎ የሚጠበቀው መጠነ ሰፊ ጥቃት የተፈራውን ቀጠናዊ ግጭት እንዳያስከትል ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል፤ በዚህ መካከል አሜሪካ በስፍራው የጦሯን አቅም ለማጠናከር የወሰደችው ውሳኔ ደግሞ ለትኩሳቱ ተጨማሪ ግለትን የሚያቀብል ነው፡፡