የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ከ40 አመታት በላይ ለኩባ ሲሰልሉ እንደነበር አመኑ
ሮቾ በዲፕሎማትነት የሰሩባቸውን ሙሉ ጊዜያቸውን በአሜሪካ ሆነው ለኩባ ሲሰልሉ ነበር የሚለው የአሜሪካ ክስ ይቀበላሉ ማለት ነው
![](https://cdn.al-ain.com/images/2024/3/01/243-171832-gettyimages-2003725973_700x400.jpg)
ዲፕሎማቱ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ይሰሩ ከነበረበት ከ1981 ጀምሮ ለኩባ አሳልፈው ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር
የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ከ40 አመታት በላይ ለኩባ ሲሰልሉ እንደነበር አመኑ።
በቦሊቪያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ለ40 አመታት ያህል ለኩባ ሲሰልሉ መቆየታቸውን አምነዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ቪክተር ማኑኤል ሮቾ የተባሉት እኝኽ የ73 አመት ዲፕሎማት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪቤት ይሰሩ ከነበረበት ከ1981 ጀምሮ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለኮሙኒስት ኩባ አሳልፈው ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
ዲፕሎማቱ በትናንትናው እለት ሀሙስ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ቀደም ሲል ይዘውት የነበረውን 'ጥፋተኛ አይደለሁም' ክርክር ቀይረውታል።
በሚቀጥለው ሚያዚያ በሚካሄደው ችሎት ዲፕሎማቱ ላይ የቅጣት ውሳኔ ይተላለፍባቸዋል ተብሏል።
ውሳኔው በአሜሪካ እና በኩባ መካከል የነበረውን ትልቁን የስለላ ጉዳይ ባልተጠበቀ ሁኔታ እንዲያበቃ ያደርገዋል።
ፍርድ ቤቱ በቀጠሮው ተላልፈው ተሰጥተዋል የተባሉትን ከባድ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ጉዳይ ለመመልከት አስቦ ነበር። ነገርግን ሮቾ፣ ጠበቃቸው እና አቃቤ ህጉ በአቤቱታው ጉዳይ ላይ ከስምምነት ሊደርሱ ችለዋል።
ዳኛ ቤት ብሉም ሮቾን ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነው እንደሆነ ለጠየቋቸው ጥያቄ "ክቡርነቶ፣ ተሰማምቻለሁ" የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ሮቾ የውጭ አጀንት ምዝገባ ስምምነትን በመተላለፍ እንደውጭ ሰላይ በማገልገል፣ መረጃ በማሳለፍ እና የአሜሪካን ፓስፖርትን ለመውሰድ ሀሰተኛ መረጃ አቅርበዋል በሚል ነው የተከሰሱት።
መርማሪዎች ሮቾ ለኩባ ለበርካታ አስርት አመታት መስራታቸውን ያመኑበትን፣ የኩባውን ፕሬዝደንት ፊደል ካስትሮን ጀግና ብለው ማድነቃቸውን እና አሜሪካን "ጠላት" ብለው መጥራታቸውን የሚያረጋግጥ ስውር የድምጽ ቅጅን ጨምሮ በርካታ ማስረጃዎችን ሰብስበዋል።
ጥፋተኝነት ማመን የብልህ ውሳኔ መሆኑን በማመን ዲፕሎማቱ እና የህግ ቡድኑ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
በዚህ መሰረት ሮቾ በዲፕሎማትነት የሰሩባቸውን ሙሉ ጊዜያቸውን በአሜሪካ ሆነው ለኩባ ሲሰልሉ ነበር የሚለው የአሜሪካ ክስ ይቀበላሉ ማለት ነው።
ሮቾ ጥፋተኝነትታቸውን በማመን ስለተባበሩ ፍርድ ቤቱ አስተያየት በሚያደርግበት ሁኔታ ውይይት አልተደረገም ተብሏል።