የኢራን አቢዮታዊ ዘብ በኢራቅ በሚገኙ የእስራኤል “የስለላ ቢሮዎች” ላይ ጥቃት ማድረሱን ገለጸ
የቴህራን ወታደራዊ ሃይል ከ90 በላይ ኢራናውያን ለተገደሉበት ጥቃት ሃላፊነት የወሰደውን አይኤስ ይዞታዎች መደብደቡንም አስታውቋል
አሜሪካ በኢራን የተፈጸሙትን የሚሳኤል ጥቃቶች “ሃላፊነት የጎደላቸው” ናቸው በሚል ተቃውማለች
የኢራን አቢዮታዊ ዘብ በኢራቅ በሚገኙ የእስራኤል “የስለላ ቢሮዎች” ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።
በከፊል ራስ ገዟ ኩርዲስታን ግዛት የተፈጸመው ጥቃት ኢራን በሶሪያ ለተገደሉባት ጀነራል የሰጠችው የመልስ ምት ነው ተብሏል።
የኢራን አቢዮታዊ ዘብ ከፍተኛ አዛዡ ሳይድ ራዚ ሙሳቪ በእስራኤል እንደተገደሉ የምታምነው ቴህራን በአጭር ጊዜ የበቀል እርምጃዋን እንደምትወስድ ስትዝት መቆየቷ ይታወሳል።
የትናንት ምሽቱ የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃትም በኢርቢል የሚገኙ የእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ ቢሮዎችን ማፈራረሱን ነው የኢራን አቢዮታዊ ዘብ ያወጣው መግለጫ የሚያሳየው።
ከኢርቢል ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ላይ ከተፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃቶች ባሻገር በሶሪያ የአይኤስ ይዞታዎችን መደብደቡንም ጠቁሟል።
በጥር ወር መጀመሪያ በከርማን ከተማ ጀነራል ቃሲም ሱሌማኒን ለማሰብ በተዘጋጀ ስነስርአት ላይ በተፈጸሙ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች 100 የሚጠጉ ኢራናውያን ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፤ አይኤስም ለጥቃቱ ሃላፊነቱን መውሰዱ አይዘነጋም።
የኢራን አቢዮታዊ ዘብ በቡድኑ ላይ የወሰደው እርምጃም የዜጎቹን ደም ለመበቀል ያለመ መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሶ ጥቃቱ እንደሚቀጥል አስጠንቅቋል።
አሜሪካ በኢርቢል በሚገኘው ቆንስላዋ አካባቢ የተፈጸመውን ጥቃት “ሃላፊነት የጎደለው” በሚል ተቃውማዋለች።
ኢራን ወደ ሰሜናዊ ኢራቅና ሶሪያ የተኮሰቻቸው ሚሳኤሎች የአሜሪካን ወታደሮች ኢላማ አለማድረጋቸውን የገለጸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ ጥቃቱ ንጹሃንን መጠበቅ አልቻለም ብሏል።
በሚሳኤል ጥቃቱ በጥቂቱ አራት ንጹሃን ህይወታቸው ማለፉና ስድስት ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል።