ሞሀመድ አል ባሺር የሶሪያ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ
ከአዲሱ እና ከቀድሞው የአሳድ ካቢኔ ጋር የመከሩት አል ባሺር እስከ መጋቢት 2025 በስልጣን ላይ ይቆያሉ ተብሏል
ሀያት ታህሪር አል ሻምን በሽብርተኝነት የፈረጀችው አሜሪካ፥ "አሳማኝ እና አካታች በሆነ ሂደት የሚመረጥ የሶሪያ መንግስትን እደግፋለሁ" ብላለች
በሶሪያ የበሽር አል አሳድ አገዛዝን አስወግዶ ስልጣን የያዘው ቡድን አዲሱን የሽግግር መንግስት የሚመሩ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር መርጧል።
በሶሪያውያን ዘንድ እምብዛም የማይታወቁት ሞሀመድ አል ባሺር እስከ መጋቢት 2025 ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በሀያት ታህሪር አል ሻም እና አጋሮቹ መመረጣቸው ተዘግቧል።
ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት ከአዲሱ መንግስታቸው እና ከቀድሞው የአሳድ ካቢኔ አባላት ጋር መክረዋል።
"ሶሪያውያን አሁን መረጋጋትን የሚያጣጥሙበት ጊዜ ነው" ያሉት አል ባሺር የተቋማት አገልግሎት እንዳይቋረጥ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እንሰራለን ብለዋል።
ሞሀመድ አል ባሺር በሰሜን ምዕራባዊ ሶሪያ ኢድሊብና አሌፖን የተቆጣጠረውን የሀያት ታህሪር አል ሻም ሀይል የመሩ ሲሆን፥ በጥር ወር 2024 ቡድኑ ያቋቋመው "የሳልቬሽን መንግስት" ወይም ኤስጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
"ኤስጂ" ልክ እንደ ሉአላዊ ሀገር መንግስት ሚኒስትሮች፣ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች፣ የፍትህና የጸጥታ ተቋማት መሪዎች እንዲኖሩት ተደርጎ የተዋቀረ ነው።
ከተለያዩ የሶሪያ ክፍሎች የተፈናቀሉ ከ4 ሚሊየን በላይ ሰዎችም በዚሁ መንግስት ስር ሲተዳደሩ ቆይተዋል።
ከአሳድ መንግስት ሃይሎች ከአሌፖ ወጥተው አገልግሎቶች ሲቋረጡ "ኤስጂ" በፍጥነት ህዝባዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ማድረጉንም ነው ቢቢሲ የዘገበው።
ኤሌክትሪካል ኢንጂነሩ ሞሀመድ አል ባሺርም ይህንኑ ስራ ሲያስተባብሩ የቆዩ ሲሆን፥ ትናንት ደግሞ ሶሪያ ወደ ህገመንግስታዊ ስርአት እስክትመለስ ድረስ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ተመርጠዋል።
ቅድሚያ የሚሰጡት ስራቸውም የተቋረጡ አገልግሎቶችን ማስጀመር መሆኑን ነው የተናገሩት።
የ13 አመቱ የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ ሚሊየን ባላይ ሶሪያውያንን ህይወት ቀጥፎ ከ12 ሚሊየን በላይ አፈናቅሏል።
የ53 አመታት የአሳድ አገዛዝ ሲያከትምም በተለያዩ ሀገራት በስደት የሚኖሩ ሶሪያውያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው።
አሳድን ከስልጣን የማንሳቱን መብረቃዊ ዘመቻ የመራው ሀያት ታህሪር አል ሻም የተሰኘው ታጣቂ ቡድን አስቀድሞ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት የነበረው ቢሆንም ስልጣን ከያዘ በኋላ አቋሙን እያለዘበ ነው።
በሶሪያ የመንግስታቱ ድርጅት ልኡክ ታጣቂዎቹ እያስተላለፉት ያለውን "መልካም መልዕክት" ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ጠይቋል።
አሜሪካም አሳማኝ እና አካታች በሆነ ሂደት ለሚመረጥ የሶሪያ መንግስት እውቅና እንደምትሰጥና እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባለስልጣናት በሶሪያ ስልጣን ላይ የሚወጣው ሃይል ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር፣ የሰብአዊ ድጋፎች ያለምንም ገደብ እንዲገቡ የሚፈቅድና ሶሪያን የሽብርተኞች መሸሸጊያ እንድትሆን የማይፈቅድ መሆን አለበት ብለዋል።
ዋሽንግተን በሶሪያ ስልጣን የያዘውን ቡድን (ሀያት ታህሪር አል ሻም) ለመደገፍ ቡድኑን ከሽብርተኞች ዝርዝር ማውጣት ይጠበቅባታል።