እስራኤል የኢራን የኒውክሌር ጣብያዎችን ለማጥቃት ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝ ተነገረ
የበሽር አላሳድን መንግስት መውደቅ ተከትሎ ቴሄራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ልታሳድግ እንደምትችል ስጋት አንዣቧል
ከ50 አመታት የአሳድ አስተዳደር ነጻ የወጣችው ሶሪያ ዳግም የእጅ አዙር ጦርነት አውድ እንዳትሆን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተንታኞች እየተናገሩ ነው
እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣብያዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝ ተገለጸ፡፡
ታይም ኦፍ እስራኤል የተባለው የእስራኤል ሚድያ ከወታደራዊ በላስልጣናት አገኘሁት ባለው መረጃ የሀገሪቱ አየር ሀይል ጥቃቱን ለማስፈጸም የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የሶሪያ አማጺያን ያልተጠበቀ የደማስቆ ቁጥጥር ቴህራን በቀጠናው ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሊያዳክመው እንደሚችል ይታመናል፡፡
ይህም ሀገሪቱ የኒውክሌር ፕሮግራሟን እንድታፋጥን ሊያነሳሳት እንደሚችል የእስራኤል መንግስት ላይ ስጋት መፍጠሩን ዘግቧል፡፡
እስራኤል እና የምእራቡ አለም ኢራን የኒውክሌር ቦንብ ለመታጠቅ እየሰራች ነው በሚል ከሚያቀርቡት ክስ በተቃራኒ ቴሄራን የአቶሚክ መርሃ ግብሯ ሰላማዊ እና ለሀይል አማራጭ የሚውል ነው ስትል ስትሞግት ሰንብታለች፡፡
የኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቅ ከማንኛውም ሀገር በበለጠ የሚያሰጋት እስራኤል ይህን ፕሮጀክት ለማስተጓጎል ከፍተኛ የኒውክሌር ተመራማሪዎችን ከመግደል ጀምሮ የተለያዩ ሚስጥራዊ ዘመቻዎችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡
በተጨማሪም የሄዝቦላ መሪ ግድያን ተከትሎ በጥቀምት ወር ከኢራን ለተፈጸመባት የሚሳኤል ጥቃት በምትሰጠው ምላሽ የኢራን የኒውክሌር ጣብያዎችን ቀዳሚ ኢላማ አድርጋ የነበረ ቢሆንም፤ የአጸፋ ምላሹ ሊፈጥረው የሚችለውን ቀውስ በመፍራት በአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ይህን እቅዷን እንደተወችው ይታወሳል፡፡
በቀጠናው የቴሄራን ዋነኛ አጋር የነበሩት በሽር አላሳድ መንግስት መውደቅ እና ወደ ሞስኮ መኮብለል ሀገሪቱ በቀጠናው ላይ ባላት ጥቅም ላይ የሚፈጥረውን ጎዶሎ ለመሙላት ወደ ኒውከሌር ጦር ማብላላት ልታዘነብል እንደምትችል የእስራኤል ወታደራዊ አመራሮች ተናግረዋል፡፡
ታይም ኦፍ እስራኤል እንደዘገበው የእስራኤል ወታደራዊ አመራሮች በቀጠናው ሌላኛው አጋር ሆኖ የሰነበተው ሄዝቦላ መዳከም እና የበሽር አላሳድ መወገድ በኢራን ላይ ለሚፈጸም ጥቃት አመቺ ጊዜ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
እስካሁን በወጡ መረጃዎች ዝርዝር የጥቃቱ ሂደቶች እና የሚፈጸመብትን ጊዜ በግልጽ አላሳወቁም፤ ነገር ግን እንደተባለው ጥቃቱ የሚፈጸም ከሆነ በቀጠናው አዲስ የተካረረ ውጥረትን ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተነገረው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቴልአቪቭ ወደ ሶሪያ ዘልቃ በመግባት ከ250 በላይ የመንግስት ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሰንዝራለች፡፡
በጥቃቱ የጦር መሳሪያ መካዘኖች ፣ የአየር መቃወሚያዎች እና የጦር መሳርያ ማምረቻዎች ኢላማ ተደርገዋል፡፡
ተንታኞች በበኩላቸው በአሜሪካ በሚደገፉ አማጽያን ከ50 አመታት የአሳድ አስተዳደር ነጻ የወጣችው ሶሪያ ዳግም የእጅ አዙር ጦርነት አውድ እንዳትሆን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ እየተናገሩ ነው፡፡