በጥናታቸው ሰዎች ነፍሳቸው ከአካላቸው ስትለይ በቅድሚያ ምን እንደሚያጋጥማቸው ያመላክታል
የሰው ልጆች ከሞት በኋላ ምን ይገጥማቸዋል የሚለው ጉዳይ አሁንም ማጠያያቁን ቀጥሏል።
ሰዎች እንደየእምነታቸው ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ ቢያምኑም ተመራማሪዎች ግን እስካሁን በሳይንሳዊ መንገድ ማረጋገጥ አልቻሉም።
በአሜሪካ ኬንታኪ ላለፉት 37 አመታት 5 ሺህ የሚጠጉ ከሞት አፋፍ ተጠግተው የተመለሱ ሰዎች ምን እንደገጠማቸው ያጠኑት ዶክተር ጀፍሪ ሎንግ “በእርግጠኝነት ከሞት በኋላ ህይወት አለ” ይላሉ።
የካንሰር ሀኪሙ ዶክተር ሎንግ ለሶስት አስርት አመታት በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ጥረት አድርገዋል።
ሞተዋል ተብለው ለቅርብ ወዳጆቻቸው መርዶ ሊነገር ሲል ነፍስ የሚዘሩ በርካቶችም ስራቸውን እንዲወዱትና ለአዲስ ምርምር እንዲዘጋጁ ያደረገ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ።
ለሞት የተቃረቡ ሰዎች ምን እንደገጠማቸው ከመጠየቅ አልፈውም የጥናት ማዕከል እስከማቋቋም ደርሰዋል።
ዶክተር ሎንግ ኢንሳይደር መጽሄት ላይ ባወጡት ጽሁፍ ከሞት የተመለሱ ሰዎች ገጥሞናል የሚሏቸውን ዋና ዋና ነገሮች አጋርተዋል።
“ብርሃናማ ስፍራ፣ ሸለቆ፣ ድልድይ፣ የሚወዱት ሰው ወይም እንሰሳን መመልከት” ለሞት ተቃርበው የሚመለሱ ሰዎች ተመለከትናቸው ብለው የሚጠቅሷቸው ጉዳዮች ናቸው።
“እነዚህ ልማዶች በባህላችን ተደጋግመው የሚነገሩ በመሆኑ ሊሆን ይችላል ብለን እንዳናምን የሚያደርገን ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት ጭምር እንዲህ አይነት ነገሮችን መመልከታቸው ነው” ሲሉም ለሞት የተቃረቡ ወይም ሞተው ዳግም ህይወት የሚዘራባቸው ሰዎች ልምድ መመሳሰል ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ ማስረጃ አድርገው ያቀርቡታል።
በጥናቱ ከተካተቱ 4 ሺህ 800 ሰዎች 45 በመቶው ሞት አፋፍ ላይ ሲሆኑ “ሰውነታቸው አይታዘዝም ወይንም ነፍሳቸው ከአካላቸው ተነጥላ ትንሳፈፋለች” ይላሉ ዶክተር ጀፍሪ ሎንግ።
ተመራማሪው ጥናታቸውን የሰዎችን ልምድ መሰረት ያደረገ እንጂ በሳይንሳዊ መንገድ የሚረጋገጥ እንዳልሆነ ያነሳሉ።
ከዚህ ቀደምም የዶክተር ሎንግን ሃሳብ የሚያጠናክሩና ከሞት በኋላ ህይወት መኖሩን የሚያመላክቱ ጥናቶች መውጣታቸውን የህንዱ ኤንዲቲቪ ዘገባ ያመላክታል።