በባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተመን የዶላር ዋጋ ስንት ብር ገባ?
ባንኮች የዶላር መሸጫ ዋጋ የቀነሱት ባንኮች የመግዣ ዋጋ ላይ ከ10 ብር በላይ ጭማሪ አድርገዋል
ኦሮሚያ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ121 ብር እየገዛ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ መሃል ያለው ልዩነት እንዲቀራረብ ባሳሰበ ማግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ ታይቷል።
ባንኮች በውጭ ምንዛሬ መሸጫ ዋጋቸው ላይ ካደረጉት ቅናሽ ባሻገር በመግዣ ዋጋቸውም ላይ ከ10 ብር በላይ ጭማሪ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ጥቅምት 7 2017 ዓ.ም የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የትናንቱን አስቀጥሏል።
በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ113.1308 ብር እየገዛ ሲሆን፤ በ115.3934 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ኦሮሚያ ባንክ ዛሬ ከፍተኛውን የዶላር መግዣ ዋጋ አቅርቧል። ባንኩ በእለታዊ የምንዛሬ ተመኑ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ121.3066 ብር እየገዛ በ123.7327 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው በእለታዊ የምንዛሬ ተመኑ ያመላከተው።
አዋሽ ባንክም ሌላኛው ከፍተኛ የዶላር መግዣ ዋጋ ያቀረበ ሲሆን፤ ባንኩ በበዛሬ ጥቅምት 7 2017 እለታዊ የምንዛሬ ተመኑ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ119.0155 ብር እየገዛ በ121.3958 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው በእለታዊ የምንዛሬ ተመኑ ያመላከተው።
ፀሃይ ባንክ ባወጣው እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ118.4265 ብር ገዝቶ በ120.7950 ብር እየሸጠ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ንብ ባንክ ባወጣው እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ115.4189 ብር ገዝቶ በ117.7273 ብር እየሸጠ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ዳሽን ባንክ የጥቅምት 7 2017 የውጭ ምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ የዶላር መግዣ ዋጋው 115.9888 ብር መሆኑን ገልጿል። 118.3086 ብር የባንኩ የዶላር መሸጫ ዋጋ ነው።