ባንኮች በዶላር መግዣ ዋጋ ላይ ከ1 እስከ 11 ብር ጭማሪ አድርገዋል
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ መሃል ያለው ልዩነት እንዲቀራረብ ባሳሰበ ማግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ ታይቷል።
ባንኮች በውጭ ምንዛሬ መሸጫ ዋጋቸው ላይ ካደረጉት ቅናሽ ባሻገር በመግዣ ዋጋቸውም ላይ ከ1 እስከ 11 ብር ጭማሪ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ጥቅምት 6 2017 ዓ.ም የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የትናንቱን አስቀጥሏል።
በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ113.1308 ብር እየገዛ ሲሆን፤ በ115 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ጸደይ ባንክ ከፍተኛውን የዶላር መግዣ ዋጋ አቅርቧል። ባንኩ በእለታዊ የምንዛሬ ተመኑ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ125.1122 ብር እየገዛ በ127.6141 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው በእለታዊ የምንዛሬ ተመኑ ያመላከተው።
ኦሮሚያ ባንክ ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ121.3066 ብር እየገዛ በ123.7327 ብር እየሸጠ መሆኑን ገልጿል።
ንብ ባንክ ባወጣው እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ115.4189 ብር ገዝቶ በ117.2583 ብር እየሸጠ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ዳሽን ባንክ የጥቅምት 6 2017 የውጭ ምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ የዶላር መግዣ ዋጋው 114.9888 ብር መሆኑን ገልጿል። 117.2886 ብር የባንኩ የዶላር መሸጫ ዋጋ ነው።