የአማራ ክልል "የሕግ የበላይነትን በማስከበር ስራ" ያላግባብ የተያዙ ካሉ ይቅርታ እንደሚጠይቅ ገለጸ
የጦር መሳሪያ ምዝገባው እስከ ግንቦት 17 እንዲቀጥል ተወስኗል
"የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራን" የራስ የቂም መወጣጫ የሚያደርጉ ካሉ እንደሚጠየቁ ተገልጿል
የአማራ ክልል የ"ሕግ የበላይነትን በማስከበር ዘመቻው" ያላግባብ የተያዙ ካሉ ይቅርታ እንደሚጠየቁና ምላሽ እንደሚሰጣቸው አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው የተጀመረው "የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር" ክልሉ ከወንጀለኞች የፀዳ እንዲሆን ነው ያሉት ዶ/ር ሰማ ከዚህ ባለፈም ዘመቻው የክልሉ ህዝብ አንድነት ኖሮት ሊመጣ የሚችልን ጠላት በብቃት እንዲመክት ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉን ሕዝብ በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመሥራት መብት ለማረጋገጥ መሆኑንም ነው የሥራ ኃላፊው ያነሱት፡፡
በክልሉ አፈና፣ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ በኃይማኖት ሰበብ ግጭት ቀስቃሽነት እና ሌሎችም ወንጀሎች በመስተዋላቸው ይህንን ለመቅረፍ ወደተቀናጀ "የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ተገብቷል" ሲሉም ገልጸዋል ዶ/ር ሰማ።
ህወሓት እና ኤርትራ ወደ ጠቅላላ ጦርነት ከገቡ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?
ከሰሞኑ በክልሉ በተጀመረው "የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ" የሚያዙ አንዳንድ አካላት መኖራቸውን ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ ግርታዎች ተፈጥረዋል፡፡ ቁጣ የተቀሰቀሰባቸው ምስራቅና ምዕራብ ጎጃምን መሰል አካባቢዎችም አሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ምላሽ የሰጡት አስተባባሪው በሕግ ማስከበር ስራው ስሕተቶች ተፈጥረው ያለ ወንጀሉ የሚያዝ ካለ ይቅርታ እንደሚደረግለትና በፍጥነት ተጣርቶ እንደሚለቀቅ ተናግረዋል፡፡
"የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ"ና በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን በሚደረገው እንቅስቃሴ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ እየተሳተፉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ወደ እንቅስቃሴ የተገባው" ከሕዝብ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ" መሆኑን ያነሱት አስተባባሪው፤ ሕዝቡ መንግሥት "የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብርለት" ሲጠይቅ ነበርም ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ማኅበረሰቡን የሚዘርፉ፣ እረፍት የሚነሱ እና ትልልቅ ከተሞችን ጭምር የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚሹ አካላትን የመለየትና በሕግ አግባብ ብቻ ወደ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማድረግ ሥራ ውስጥ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ በክልሉ ስለተጀመረው የጦር መሳሪያ ምዝገባም አንስተዋል ዶ/ር ሰማ፡፡
ምዝገባው መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ሕዝቡ በጀግንነት ታግሎ ከጠላት የማረከውን መሳሪያ በሕጋዊ መልኩ አስመዝግቦ እንዲይዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጦር መሳሪያ ምዝገባው ከሕዝብ የተሰወረ ምንም አይነት ሌላ ዓላማ እንደሌለውም ነው አስተባባሪው የጠቆሙት፡፡
አሁንም ቢኾን "ጠላት" በወረራ የያዛቸው የክልሉ አካባቢዎች በመኖራቸውና የጦርነት ጉሰማው ባለመብረዱ ሕዝቡ በእጁ የያዘውን ትጥቅ አስመዝግቦ ራሱንና ወገኑን ለመጠበቅ እንዲያውለውም አሳስበዋል።
አሁን ላይ በርካቶች የጦር መሳሪያ እያስመዘገቡ መሆኑን የገለጹት ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ምዝገባው መጠናቀቅ ባለመቻሉ ረቡዕ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲቀጥል ተወስኗል ብለዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ን ወክለው ፓርላማ የገቡ አባላት በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ነው ያሉት "መንግስታዊ እገታና ስወራ" በአስቸኳይ እንዲቆም ትናንትና ባወጡት መግለጫ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡