የመንግስት ተቋማት አለመተባበር ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራን መንግስት እንዳፈናቸው ማሳያ ነው ሲሉ ባለቤታቸው ተናገሩ
ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ሰኞ ዕለት 5 ሰዓት አካባቢ ከቤት እንደወጡ አለመመለሳቸውን ወ/ሮ መነን ገልጸዋል
ወ/ሮ መነን የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች የብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ጉዳይ “እኛን አይመለከትም” የሚል መልስ እንደሰጧቸው ተናግረዋል
የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞን ከመንግስት ውጭ ማንም ሊያፍናቸው እንደማይችል ባለቤታቸው ተናገሩ፡፡
ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኃይሌ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ መንግስት እንጅ ማን ሊያፍነው ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ መነን ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ከታፈኑ በኋላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደው መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ወደ ፌዴራልና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ማምራታቸውን ቢገልጹም ሁለቱም ተቋማት “እኛን አይመለከትም” እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ መነን በዛሬው እለት ወደ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ቢያመሩም ሊተባበሯቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል መሪውን ማን ሊያፍናቸው ይችላል? በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ሮ መነን “መሃል አዲስ አበባ ላይ ከመንግስት ውጭ ማን ሊያፍነው ይችላል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ከታፈኑ በኋላም እንዲተባበሯቸው የጠየቋቸው የመንግስት ተቋማት አለመተባበራቸው ሲጨመርበት ብርጋዴር ጀነራል ተፈራን መንግስት እንዳፈናቸው ያሳያልም ሲሉ አክለዋል ወይዘሮ መነን፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ውስጥ ከቤታቸው እንደወጡ አለመመለሳቸውን ያነሱት ባለቤታው ወ/ሮ መነን ኃይሌ አሁንም ወደተለያዩ ተቋማት እየተዘዋወሩ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራን ሰኞ ዕለት ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም 5 ሰዓት አካባቢ ከቤት የወጡት ከቀድሞው የፌዴራል እና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ዮሐንስ ቧያለው ጋር ቀጠሮ እንዳላቸው በመግለጽ እንደነበር ወ/ሮ መነን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀጠሮ በኋላ ግን ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም ብለዋል ባለቤታቸው፡፡
ብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከ 10 ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ “ውጥን አላቸው” በሚል ክስ ተከሰው እስር ላይ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ለሁለት ጊዜያት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ በመሆን ያገለገሉት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ሳተላይት ራዲዮና ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጋር ቃለ ምልልስ ነበራቸው፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ለመጨረሻ ጊዜ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ በመሆን የተሾሙት ባለፈው ሃምሌ ነበር፡፡ ከሹመት በኋላም የፌደራል መንግስት ከህወሃት ጋር ባደረገው ጦርነት በፌደራል መንግስት ጦር እዝ ስር በመሆን ውጊያ ሲመሩ፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
አል ዐይን አማርኛ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በብርጋዴር ጄ/ል ተፈራ ማሞ መታገት ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥረት ቢያደርግም ኃላፊዎቹ ስልክ ማንሳት ባለመቻላቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡
የፌደራል መንግስት እስካሁን ድረስ ስለብርጋዴር ጀነራል ተፈራ መታፈን ጉዳይ በይፋ ያለው ነገር የለም፡፡