አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ያሳስበኛል አለች
አምባሳደር ማስኛ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች መፍቻው ብቸኛው መንገድ ንግግር ነው ብለዋል

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማስኛ የአዋጁ መራዘም እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል
አሜሪካ በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘሙ በእጅጉ ያሳስበኛል ብላለች።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማስኛ በኢምባሲው የፌስቡክ ገጽ ባወጡት አጭር መግለጫ የአዋጁ መራዘም እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።
አምባሳደር ማስኛ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች መፍቻው ብቸኛው መንገድ ንግግር ነው ብለዋል።
የአምባሳደሩ መግለጫ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ጉዳይ ከሚያወጣቸው መግለጫዎች ጋር የሚመሳሰል ነው።
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በትናንትናው እለት ባካሄደው ስብሰባ ባለፈው ሐምሌ ወር ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአራት ወራት ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቆታል።
መንግስት በአማራ ክልል እና እንደአስፈላጊቱ በሌሎች ቦታዎች ተፈጻሚ ይሆናል ያለውን አዋጁ ያወጀው፣ በአማራ ክልል ከልዩ ኃይል መፍረስ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ግጭት በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር እንደማይችል በመግለጽ ነበር።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፋኖ ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቅን ጨምሮ በርካታ ውጤቶችን እንዳመጣ የገለጸው መንግስት "የቀሩ ስራዎች" በመኖራቸው ምክንያት ማራዘም መፈለጉን ገልጿል።
መንግስት አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱን ቢገጽም፣ አሁንም በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንዳልቆም የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
በግጭቱ አውድም በርካታ ንጹሃን ግድያ እና የመቁሰል አደጋ እንደሚደርሰባቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጨምሮ የሰብአዊ መብት ተቋማት በርካታ ጊዜ ሪፖርት አውጥተዋል።
የኢሰመኮ ከሚሽነር ዶክተር ዳኒኤል በቀለም በትናነትናው እለት በኤክስ ገጻቸው የአዋጁ መራዘም ያሳስበኛል ብለዋል።
“የአዋጁ መራዘም በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ አሳሳቢ ነው”።
ገዥው ፖርቲ ብልጽግና በቅርቡ ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ መንግስት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ነገርግን ፖርቲው ከየትኛው ታጣቂ ቡድን ጋር እና በምን ሁኔታ የሚለውን ጉዳይ አላብራራም።