የክልሉ ከተሞች በሀገር መከላከያ ቁጥጥር ስር ሲሆኑ ገጠሩ ክፍል ደግሞ በፋኖ ታጣቂዎች መያዛቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል
በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ ይሆን?
ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ ለማደራጀት ወስኛለሁ ማለቱን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው፡፡
ይህ ግጭት ቀስ በቀስ እያደገ መጥቶ ወደ ጦርነት የተቀየረ ሲሆን የቀድሞው የክልሉ መንግስት በመደበኛ የክልሉ የጸጥታ ሀይል ህግ ማስከበር እንደማይችል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሀምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡
ለስድስት ወራት ይቆያል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጠናቀቂያ ጊዜው የደረሰ ሲሆን ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም አዋጁ ስድስት ወራት ይሞለዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ምን ይመስል ነበር?፤ ህይወት በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ እንዴት ነበር? ሲል በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ያሉ ነዋሪዎችን ቃል መጠይቅ አድርጓል፡፡
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ እንዳሉን “በማንኛውም ሰዓት እና ቀን እንደልባችን ስንቀሳቀስባት የነበረችው ጎንደር ከተማ አሁን ጸሎታችን ሁሉ በህይወት እንድንኖር ብቻ ሆኗል“ ብለውናል፡፡
ካለፈው ሀምሌ እና ነሀሴ ጀምሮ በየቀኑ በተባራሪ ጥይት እና በከባድ መሳሪያ ተኩስ ሰው እየሞተ ነው የሚለን ይህ ነዋሪ በህይወት ያለነው ደግሞ ጥይቱ ቢስተን በረሃብ እና በጭንቀት ማለቃችን ነው ብሏል፡፡
እንደ ነዋሪው ገለጻ ከሆነ በየጊዜው በከተማው መግቢያ እና መውጫ ድንገት በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ተኩስ ሲጀመር ንጹሃንም እየተገደሉ፣ ትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎቶች እንደሚቋረጡ ነግሮናል፡፡
ስቃይን እና በችግር ውስጥ መኖርን እንድንለማመድ ተደርገናል የሚለው ይህ አስተያየት ሰጪ አሁን ላይ ነዋሪው መቼም ቢሆን ድንገት የሆነ ቦታ ውጊያ እንደሚጀመር፣ ከዚያ ትንሽ ረገብ ሲል ደግሞ መደበኛ ኑሮውን መቀጠል ተላምዷል ብሏል፡፡
ጦርነቱን እያደረጉት ያሉት አካላት አንዳቸው አንዳቸውን እንደሚያሸንፉ በተለያየ መንገድ ሲናገሩ እንደሚሰማ የተናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ ይህ ጦርነት አሸናፊ እሚኖረው አይመስለኝም ሲል አክሏል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ሲሆን በአማራ ክልል አስቸኳይ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ሰዎች እየተገደሉ እና በጅምላ እየታሰሩ ሀዘኑ በየቤቱ መግባቱን ገልጿል፡፡
ቀበሌ 14 አቡነ ሀራ እሚባል ቤተ ክርስቲያን በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተገድለው 24 ሰዎች ባንድ ቀን ሲቀበሩ አይቻለሁ የሚለው ይህ የባህርዳር ከተማ አስተያየት ሰጪ ነዋሪው የስቃይ ህይወት እየገፉ እንደሆነም ነግሮናል፡፡
ዉጊያ ቆመ ትንሽ ሰላም ወረደ ብለን ስንተኛ ድንገት በራችን ተንኳኩቶ የጸጥታ ሀይሎች መሆናቸውን እንኳን ሳይናገሩ እና እነማን እንደሆኑ ሳይነግሩን ፍተሻ ነው የመጣነው ይባላል፣ ንብረት ይወሰዳል ሰዎች በጅምላ ይታሰራሉ አጸያፊ ስድቦችን ይሰድቡናልም ብሏል፡፡
አስቸኳይ አዋጁ ሰዎች እንደልባቸው የፈለጉትን ቤት እንዲፈትሹ እና እንዲዘርፉን ለትንሹም ትልቁም ጉቦ እንድንከፍል እድል ሰጥቷል የሚለው ይህ ነዋሪ ጉዳዩ ከዚህም በላይ ሳይከፋ መፍትሔ እንዲፈለግለት ጠይቋል፡፡
“የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች ልጆቻችሁ ፋኖን ተቀላቅለዋል፣ ፋኖ ደግሞ ቤተሰባችሁ ሚሊሻ ሆኖ ከመንግስት ጋር ወግኖ እየገደለን ነው በሚል ህዝቡን እያሰቃዩ ነው” ያለን ደግሞ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የእናርጅ እናውጋ ወረዳ ነዋሪ ነው፡፡
እናርጅ እናውጋ ወረዳን ጨምሮ ከአብዛኞቹ የጎጃም አካባቢዎች ወደ ደብረ ማርቆስ፣ ባህርዳር እና አዲስ አበባ መጓዝ የማይቻል ሆኗል የሚለን ይህ ነዋሪ ህዝቡ በጥይት እና ኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነውም ብሏል፡፡
እንደ ነዋሪው አስተያየት ከተሞች ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሲሰፍር የከተሞች ዙሪያን ጨምሮ የገጠር ቀበሌዎች በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ከዋሉ ወራቶች መቆጠራቸውንም አክሏል፡፡
የወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ትውልድ ስፍራ በሆነችው ገደብ ቀበሌ ብቻ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ የመከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ታጣቂዎች ባካሄዱት ከባድ ውጊያ 16 ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋልም ብሏል፡፡
በሌላ ቀን በተካሄደ ሌላ ውጊያ ደግሞ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ላይ የነበሩ ንጹሃንን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ እና ነዋሪዎች በቤታቸው እያሉ መገደላቸውንም ይሄው ነዋሪ ጠቅሷል፡፡
በውጊያው የሐገር መከላከያ ሰራዊት ጉዳት ከደረሰበት ሰራዊቱ ወደ ንጹሃን ዜጎች መኖሪያ መንደር በመግባት በቀል እንደሚፈጸም የሚናገረው ይህ አስተያየት ሰጪ ህዝቡ ከባድ ስቃይ ውስጥ እንዳለም አክሏል፡፡
አሁን ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በወረዳዋ ዋና ከተማ ደብረወርቅ ላይ ሆነው የቤት ለቤት ፍተሸ በተደጋጋሚ እንደሚካሂዱ፣ የጦር መሳሪያን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች ከነዋሪው እየተወሰዱ እንደሆነም ነግሮናል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ነዋሪ ሲሆን ወረዳው ከደቡብ ወሎ ጃማ እና ደጎሎ ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ስር ካለው ደራ እና መራቤቴ ወረዳዎች ጋር የሚዋሰን በመሆኑ በተደጋጋሚ ውጥረት እየተከሰተበት ነው ብሎናል፡፡
እንደ ነዋሪው ገለጻ ከሆነ የመንግስት ተቋማት ክፍት ቢሆኑም የተቋማት አመራሮች እንደሌሉ፣ ሰራተኞች ደግሞ ተገልጋይ ከመጣላቸው እንደሚያገለግሉ ነገር ግን ለደመወዛቸው ሲሉ ገባ ብለው ፊርማ ብቻ ፈርመው እንደሚሄዱም ነግሮናል፡፡
በተለይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማዋ ከገባ ህዝቡ ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ፍራቻ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እንደማይልክ፣ ሰራተኞችም ከቤታቸው እንደማይወጡ የነገረን አስተያየት ሰጪው ይህ የሚሆነው የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የህዝብ መገልገያ ተቋማትን እንደ መጠለያ እና ካምፕ ስለሚጠቀሙ ነውም ብሏል፡፡
የሚዳ ወረሞ አጎራባች ወረዳ የሖነው መራቤቴ ዓለም ከተማ እና ዙሪያ ወረዳው ካሳለፍነው ሰኔ 2015 ዓ.ም ጀምሮ መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተማቸው እንዳልገባ እና ህዝቡ በራሱ ያለምንም ችግር እየተዳደረ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
በአካባቢው በተደጋጋሚ በሚፈጸም የድሮን ጥቃት ምክንያት ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ እና አካላቸው እንደጎደለም ከዚሁ ነዋሪ ሰምተናል፡፡
በደቡብ ወሎ የመርሳ ከተማ ነዋሪ የሆነ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩሉ በሀገር መከላከያ እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚደረገው ጦርነት ንጹሀን ዋጋ እየከፈሉ ነው ብሏል፡፡
በተለይም መኖሪያ መንደሮች ላይ ከባድ መሳሪያዎች እየተተኮሱ ንጹሀን ዜጎች እየተገደሉ ነው ያለው ይህ አስተያየት ሰጪ ሰዎች በገፍ እንደሚታሰሩ፣ ማንም ሳይጠይቃቸው ከወር በላይ እንደሚቆዩ፣ ለምን እንደታሰሩ እና ለምን እንደተፈቱ የማይነገራቸው ሰዎች እንዳሉም ነግሮናል፡፡
አስተያየት ሰጪዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች እና በተጨማሪ ጉዳዮች ዙሪያ የመንግስትን ምላሽ ለማካተት የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም አስቸኳይ ጉዳይ ላይ እንደሆኑ፣ ቆይተን እንድንደውል ከነገሩን በኋላ ደግመን ብንደውልም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡
እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተነሱበት ቅሬታዎች ዙሪያ ምላሹን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ በበኩላቸው አስፈጻሚው እስካሁን በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ ወይም ይራዘም የሚለውን ጉዳይ እንዳላቀረበላቸው ነግረውናል፡፡
“የአስቸኳይ አዋጁ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ገና ስለሆነ ምን አልባት እየተገመገመ ሊሆን ይችላል” ያሉን ፕሮፌሰር ምህረቱ ጉዳዩን የማቅረብ ሀላፊነቱ የአስፈጻሚው አካል ነውም ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር እና የፌደራል መንግስት ከዚህ በፊት በሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ተመድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በርካታ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት እና ሀገራት በአማራ ክልል ያለው የንጹሃን ዜጎች ጉዳት እንዲቆምም አሳስበዋል፡፡
ተፋላሚ ወገኖችም ከጦርነት ይልቅ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ መንግስትም ንጹሃንን ከማንኛውም ጥቃት እንዲጠብቅ እና የድሮን ጥቃቱን እንዲያቆም እነዚሁ ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከአንድ ወር በፊት በሰጡት መግለጫ በአማራ ክልል የድሮን ጥቃቱ ህዝብን በማይጎዳ መንገድ ትክክለኛውን ኢላማ ስናገኝ እንጠቀማለን ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡