ቻይና በበኩሏ ማዕቀቡ አሜሪካንንም ይጎዳል ብላለች
አሜሪካ በ30 የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የዓለም አንደኛ እና ሁለተኛ ልዕለ ሀያል የሆኑት ሀገራት የሆኑት አሜሪካ እና ቻይና የንግድ ጦርነት ከጀመሩ ቆይተዋል።
ቻይና በወታደራዊ ቴክኖሎጂ በአሜሪካ ላይ የበላይነትን መውሰዷ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን እንዳሳሰበ ሮይተርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ዲሞክራት እና ሪፐብሊካን ፓርቲ ሴናተሮች ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቻይና ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ሲወተውቱ ነበርም ተብሏል።
በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቻይናውን ግዙፉ የሚሞሪ አምራች ኩባንያ የሆነው ያንትዝ ቴክኖሎጂ ኩባንያን ጨምሮ በ30 ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
ዋሸንግተን ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለቻይና ወታደራዊ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የማይክሮ ቺፕስ ምርቶቻቸውን እንዳይሸጡም እገዳ ጥለዋል።
አሜሪካ እና ቻይና ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቤጂንግ ጋር የንግድ ጦርነት ጀምረው ነበር።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየሻከረ የመጣ ሲሆን በታይዋን ጉዳይ ወደ ጦርነት እንዳያመሩም ተሰግቷል።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ቻይና ከአሜሪካ ጋር በወታደራዊ ደህንነት እና አየር ንብረት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ላለመስራት መወሰኗን አስታውቃለች።
አሜሪካ ቻይና ከሩሲያ እና ኢራን ጋር ባላት ግንኙነት ደስተኛ እንዳልሆነች የገለጸች ሲሆን በተለይም የሩሲያን ነዳጅ መግዛቷን እንድታቆም በመወትወት ላይም ትገኛለች።