ቻይና፤ ታይዋንን በጎበኙት የሊቱያኒያ ምክትል ሚኒስትር ላይ ማዕቀብ ጣለች
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ “ የምክትል ሚኒስትሯ ጉብኝቱ የአንድ ቻይናን መርህ የሚጻረር ነው” ብሎታል
በቻይና ውሳኔ የደነገጡት የሊቱያኒያ ምክትል ሚኒስትር በበኩላቸው “በቻይና መግለጫ አዝኛለሁ” ብለዋል
ቻይና፤ ታይዋንን በጎበኙት የሊቱያኒያ ምክትል የትራንስፖርት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አግኔ ቫይሲዩኬቪቺዩት ላይ ማዕቀብ ጣለች።
በሊቱያኒያ ምክትል የትራንስፖርት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አግኔ ቫይሲዩኬቪቺዩት የተመራው 11 ልዑካን ያካተተው ቡዱን እንደፈረንጆቹ ነሃሴ 7 ቀን 2022 በታይዋን በነበረው ቆይታ፤ የታይዋን ንፕሬዝዳንት ጨምሮ የተለያዩ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በመመካከር የሊቱያኒያ-ታይዋን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጠናከርበት ዙሪያ ተወያይቷል።
ሆኖም ግን የልዑካን ቡድኑ ቆይታ ለቻይና ምቾት የሚሰጥ ሆኖ አልተገኘም።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ጉብኝቱ የአንድ ቻይናን መርህ የሚጻረር፣ በቻይና የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገባ፣ የቻይናን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጎዳ ነው” ብለዋል።
ሚኒስቴሩ፤ ቻይና ከሊቱያኒያ የትራንስፖርት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር የምታደርገውን ማንኛወም ትብብር እንዳቋረጠችም ይፋ አድርጓል።
በቻይና ውሳኔ የደነገጡት የሊቱያኒያ ምክትል የትራንስፖርት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሯ አግኔ ቫይሲዩኬቪቺዩት በቻይና መግለጫ አዝኛለሁ ብሏል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ፤ ቤጂንግ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገር ላይ የሚወሰደውን ህገ ወጥ እርምጃ ለመቀጠል እና ለማጠናከር አቅዳ እየተንቀሳቀሰች ነው።
በቅርብ ወራት ውስጥ በሊቱያኒያ እና በቻይና መካከል ውጥረት ነግሷል።
በተለይም ሊትዌኒያ፤ ታይዋን በሊትዌኒያ ዋና ከተማ ቪልኒየስ በስሟ የተወካይ ቢሮ እንድትከፍት ከፈቀደች በኋላ የሀገራቱ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ ይነገራል።