የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀማር ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው
የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀማር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
ማይክ ሀመር ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሱዳን ጉዳይ ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ህበረት ጋር ይመክራሉ ብሏል መግለጫው
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀማር ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው።
የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀማር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በድህረ ገጹ ባወጣው መግለጫ ማይክ ሀማር ከፈረንጆቹ መስከረም 3-13 ባለው ጊዜ ውስጥ ቤልጄየምን፣ ኬንያን እና ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ብሏል። ነገርግን መግለጫው ማይክ ሀማር ሶስቱን ሀገራት እንደሚጎበኙ ከመግለጽ ወጭ የትኛውን ሀገር መቼ እንደሚጎበኙ ወይም ጉብኝታቸው ከየት እንደሚጀምር ግልጽ አላደረገም።
ማይክ ሀመር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ የዘላቂ ስምምነት አፈጻጸም እንደሚገመግሙ መግለጫው ጠቅሷል።
ማይክ ሀመር ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሱዳን ጉዳይ ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ህበረት ጋር ይመክራሉ ብሏል መግለጫው።
አሜሪካ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ፣ እንዲበተኑ እና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ በማድረግ፣ ተፈናቃዮች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ በማድረግ፣ የሽግግር ፍትህን እና ተጠያቂነትን በማጠናከር እና በሌሎች መንገዶች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የፌደራል መንግስቱን እና ህወሓትን ለመርዳት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።
መግለጫው ከፕሪቶሪያው ስምምነት በተጨማሪ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭትም በሰላም በሚቋጭበት ሁኔታ ከባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ብሏል።
አሜሪካ በሁለቱ ክልሎች ያሉ ግጭቶች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ አዲስ አበባ ባለው ኢምባሲዋ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል በተደጋጋሚ መግለጫ አውጥታለች።
የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች፣ በኦሮሚያ ክልል "ሸኔ" ተብሎ በሽብር ከተፈረጀው ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ለአመታት፣ በአማራ ክልል ደግሞ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ከባለፈው አመት ሚያዝያ ጀምሮ የትጥቅ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለማስቆም መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ የጸጥታ ኃይል ያሰማራ ቢሆንም ግጭቱ አልቆመም።
በክልሉ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እና ከግጭቱ አውድ ውጭ በርካታ ንጹሃን በዋናነት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየተገደሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) ጨምሮ በርካታ አለምአቀፍ የመብት ተቆርቋሪ ተቋማት ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።