ማይክ ሀመር የአማራ ክልል ግጭት በንግግር ስለሚፈታበት ሁኔታ እንደሚመክሩ ተገለጸ
ማይክ ሀመር በብራሰልስ በኢትዮጵያና ሱዳን ጉዳይ ከአውሮፖ ህብረት ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል
አምባሳደር ሀመር ከባለስልጣናቱ ጋር የፕሪቶሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት ሙሉበሙሉ እንዲተገበር በሚያደርጉት ድጋፍ ዙሪያ እንደሚወያዩም ሚኒስቴሩ ገልጿል
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ማይክ ሀመር በብራሰልስ በኢትዮጵያና ሱዳን ጉዳይ ከአውሮፖ ህብረት ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ማይክ ሀመር በአውሮፖ በፈረንጆቹ ከነሐሴ 19-26 የሚቆዩ ሲሆን ወደ እዚያ ያቀኑት የዓለም የውሃ ሳምንት ስብሰባ ላይ ለመካፈል ነው።
ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በንግግር መፍትሄ ስለሚያገኝበት ሁኔታ በብራሰልስ ይመክራሉ ብሏል።
ማይክ ሀመር በአሮሚያ ያለውም ግጭትም በተመሳሳይ በንግግር እንዲፈታ እንደሚመክሩ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደር ሀመር ከባለስልጣናቱ ጋር የፕሪቶሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት ሙሉበሙሉ እንዲተገበር በሚያደርጉት ድጋፍ ዙሪያ እንደሚወያዩም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በአማራ ክልል የመንግስትን የልዩ ኃይል የማፍረስ እና "መልሶ የማደራጀት" ውሳኔ ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ክልሉ ወደ አለመረጋጋት ውስጥ ገብቷል።
ከሳምንታት በፊት የፌደራል መንግስት በክልሉ በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን እና ይህንን በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርአት መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን ማስታወቁ ይታወሳል።
መንግስት በወሰደው እርምጃ የተወሰኑ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ነበር ያላቸውን ታጣቂ ኃይሎች ከበርካታ ከተሞች ማስወጣቱን እና ከተሞቹም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን ገልጾ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ከትላልቅ ከተሞች ራቅ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች መቀጠላቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ናቸው።
በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት በተካሄደባቸው በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በንጹሃን ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት መግለጹ ይታወሳል።
መንግስት ዝርዝር ሁኔታ ግልጽ ባያደርግም ችግሩን በሰላም ለመፍታት እድሉ እንዳለ ገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል ያለው ግጭት እንዲቆም እና ችግሩ በንግግር እንደፈታ ጥሪ አቅርቧል።