ማይክ ሀመር ግጭቱ በድርደር ስለሚፈታበት ሁኔታ ለመመካከር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ተገለጸ
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ወደ ናይሮቢ እና አዲስ አበባ በመምጣት ከኬንያ እና ኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ከፈረንጆቹ ነሐሴ 28 እስከ መስከረም 8 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ናይሮቢ እና አዲስ አበባ በመምጣት ከኬንያ እና ኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ማይክ ሀመር በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች "እየተካሄደ ያለው ግጭት" በድርድር መፍትሄ በሚያገኝበት ሁኔታ እንደሚመክሩ ሚኒስቴር ገልጿል።
ሚኒስቴሩ እንዳለው ማይክ ሀመር የሚመጡት በግጭቱ ሰላማዊ ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ እንዳይሆኑም ለማሳሰብ ጭምርም ነው ብሏል።
የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት አሰማርቷል።
በክልሉ በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ መኖሩን እና ይህንንም በመደበኛው ስርአት መቆጣጠር እንደማይቻል በመግለጽ ነበር መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው።
መንግስት በወሰደው "የህግ ማስከበር" እርምጃ በርካታ የክልሉ ከተሞችን ከታጣቂዎች ስጋት ነጻ ማድረጉን እና የጸጥታው ችግር መቀልበሱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕዝ መምሪያ መግለጹ ይታወሳል።
ምንምእንኳን ትላልቅ ከተሞች ወደ ሰላም መሆናቸውን ቢገልጽም በአንዳንድ ከተሞች ግጭት ማገርሸቱን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ናቸው።
በክልሉ ከትላልቅ ከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች መኖራቸው እየተነገረ ነው።
በግጭቱ ንጹሃን ሰዎች የሞት እና የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል።
ግጭቱ እንዲቆም እና ችግሩ በንግግር እንዲፈታም ኢሰመኮ አሳስቦ ነበር።