የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት ቲክቶክን በመላው ሀገሪቱ ሊያግድ የሚችል አዋጅ አጸደቀ
አዋጁ ቲክቶክ በስድስት ወራት ውስጥ አክሲዮኖችን ለአሜሪካውያን የማይሸጥ ከሆነ በሀገሪቱ እንዳይሰራ ይታገዳል ይላል
በዋይትሃውስ ቆይታቸው ቲክቶክን ለማዘጋት ጥረት ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አዋጁን ተቃውመዋል
የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት ቲክቶክን በመላው ሀገሪቱ ሊያግድ የሚችል አዋጅ አጸደቀ።
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በስድስት ወራት ውስጥ አክሲዮኖችን ለአሜሪካውያን ካልሸጠ በመላው አሜሪካ ይታገዳል ይላል አዋጁ።
አዋጁ በሴኔቱ ጸድቆ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካልተፈረመበት ግን ህግ ሆኖ ተፈጻሚ አይሆንም ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ባይደንም የህግ መወሰኛ ምክርቤቱ (ሴኔቱ) አዋጁን ካጸደቀው ሳይውሉ ሳያድሩ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩበት መግለጻቸው ይታወሳል።
በ2012 የተቋቋመው ቲክቶክ የንግድ ፈቃዱ በካይማን ደሴቶች ነው የተመዘገበው፤ በአውሮፓ እና አሜሪካም በርካታ ቢሮዎች አሉት።
በአለማቀፍ ደረጃ በወር ከ1 ቢሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን ያፈራው የቻይናው መተግበሪያ በአሜሪካም ከ150 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት።
የዋሽንግተን ባለስልጣናት ግን መተግበሪያው የግለሰቦችን ሚስጢር ለቤጂንግ አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል በሚል የተለያዩ ክሶችን በማቅረብ በመንግስት ተቋማት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል እስከማገድ ደርሰዋል።
የቲክቶክ እናት ኩባንያ ባይትዳንስ በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የጸደቀውን አዋጅ ተፈጻሚ ለማድረግ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት ቢቢሲ ዘግቧል።
የአሜሪካውያን የቲክቶክ ተጠቃሚዎች መረጃ በቻይና ከሚገኙ የባይትዳንስ ኩባንያ ሰራተኞች ጋር እንዳይገናኝ መደረጉን የሚጠቅሱት የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሹ ዚ ቸው፥ መተግበሪያውን ከመረጃ ምንተፋ ለመጠበቅ የተሰሩ ስራዎችን የአሜሪካ ኮንግረስ ድረስ በመዝለቅ ማብራራታቸው አይዘነጋም።
ዋና ስራ አስፈጻሚው የአሜሪካ ሴኔት አዲሱን አዋጅ የሚያጸድቅ ከሆነ ይበልጥ የሚጎዱት በቲክቶክ ስራ ያገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ናቸው ብለዋል።
በቲክቶክ ገንዘብ የሚሰሩ በርካታ አሜሪካውያንም የአዋጁን መጽደቅ ተቃውመው አደባባይ መውጣታቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አሜሪካ የምታቀርበው ወቀሳ መሰረተ ቢስ መሆኑን በመጥቀስ፥ ውንጀላው የንግድ ፉክክርና ኢንቨስትመንትን የማያበረታታ ነው ብሏል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በቲክቶክ ላይ የከፈቱት ዘመቻ በትልልቆቹ የሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጭምር የሚደገፍ መሆኑንም ቤጂንግ ስትገልጽ ይደመጣል።
በዋይትሃውስ ቆይታቸው ቲክቶክ በአሜሪካ እንዲታገድ ጥረት ያደረጉትና በቀጣዩ ምርጫ ከጆ ባይደን ጋር የሚፎካከሩት ዶናልድ ትራምፕ አዲሱን ረቂቅ አዋጅ ተቃውመዋል።
ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ ከሆኑትና በባይትዳንስ መጠነኛ አክሲዮን ካላቸው ጄፍ ያስ ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው ሃሳባቸውን የቀየሩት።
አንዳንድ ዴሞክራቶችም ቢሆኑ ቲክቶክን የሚያዘጋ ውሳኔ ወጣት መራጮችን ሊያሳጣን ይችላል በሚል ተቃውሞ እያሰሙ ነው ተብሏል።