ቴህራን በበኩሏ ዋሽንግተን “ከወራሪ ጋር በማበርና የንጹሃን ፍልስጤማውያን ደም በማፍሰስ” ጦርነቱን እያባሳሰች ነው ብላለች
አሜሪካ እስራኤልና ሃማስ ጦርነት አድማሱን እንዳያሰፋ እንደምትፈልግ ገለጸች።
ከቴል አቪቭ ጎን የተሰለፈችው ዋሽንግተን ለፍልስጤሙ ሃማስ እና ለሊባኖሱ ሄዝቦላህ ድጋፍ ከምታደርገው ኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትሻም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን የተናገሩት።
ሚኒስትሩ ትናንት በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ዙሪያ በተጠራው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ፥ ቴህራን በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ከነካች ግን ፈጣን ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ዝተዋል።
አሜሪካ ኢራን እና አጋሮቿ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል ከ2 ሺህ በላይ ወታደሮች፣ ተዋጊ ጄቶች እና አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ መርከቦችን ወደ እስራኤል ልካለች።
በመንግስታቱ ድርጅት የኢራን አምባሳደር አሚር ሳይድ ኢራቫኒ በበኩላቸው፥ ብሊንከን በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ውስጥ ኢራንን “በመሰረተቢስ ውንጀላ” ለመክሰስ መሞከራቸውን ተቃውመዋል።
“በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁርጠኛ ነን፤ አሜሪካ ግን ከወራሪ ሃይል ጋር በማበርና የፍልስጤማውያን ንጹሃን ደም በማፍሰስ ግጭቱን እያባሳሰች ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
የዮርዳኖሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጦርነቱ ወደ ዌስትባንክ፣ ሊባኖስ እና ሌሎች ግንባሮች እየተስፋፋ መሄዱ እንደማይቀር ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በጋዛ ሰርጥ “ግልጽ የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል” ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በመንግስታቱ ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኢርዳን የዋና ጸሃፊውን ንግግር “አስደንጋጭ” ነው ያሉት ሲሆን፥ በፍጥነት ሃላፊነታቸውን እንዲለቁም በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ጥሪ አቅርበዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሊ ኮሀን ሚዛናዊ አስተያየት አልሰጡም ካሏቸው ጉቴሬዝ ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት መሰረዛቸውን ነው ያስታወቁት።
አሜሪካ 19ኛ ቀኑን የያዘው ጦርነት እንዲረግብ ፍላጎት እንዳላት ስትገልጽ ብትቆይም በትናንትናው እለት ከተለያዩ ሀገራት የቀረበውን በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረስ ጥያቄ ሳትቀበለው ቀርታለች።
በጋዛ ሰርጥ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የተኩስ ድምጽ እንዳይሰማ እንጂ ዘላቂነት እና ተጠያቂነት ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት እንደሌላት አሳይታለች።