አሜሪካ እና ኬንያ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ የቆዩ ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንክን እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በኢትዮጵያ ጉዳይ መምከራቸው ተገለጸ፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በሰጡት መግለጫ ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው የስልክ ቆይታ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተመለከተ ተወያይተዋል ብለዋል፡፡
አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር አብቅቶ ሁሉም ወገኖች ወደ ጠረጴዛ መጥተው ለድርድር እንዲቀመጡ በአፍሪካ ህብረት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ አንደሆነች በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ የሚታወቅ ነው፡፡
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እያደረጉት ያለውን ጥረት የዚህ አካል እንደሆነም እሙን ነው፡፡
ኬንያም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ስትገልጽ የምትደመጥ ሀገር ናት፡፡
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስባቸው በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ከፍራንስ-24 ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጉዳይ መፍትሄ እንዲያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተሰምተዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው ማንኛውም ነገር ወደ ኬንያ ይደርሳል” ያሉት ዊሊያም ሩቶ፤ ግጭቱ መፍተሄ እንዲያገኝ ኬንያ የራሷን ሚና ትጫወታለችም ብለዋል፡፡
አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቀናት በፊት በነበረው በዓለ ሲመታቸው በኢትዮጵያ እና በታላላቅ ሐይቆች ቀጠና (ግሬት ሌክስ) ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚያከናውኑትን ተግባር እንደሚቀጥሉ መናጋራቸው ይታወሳል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው አንድ ወር ብቻ የቀረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ድጋሚ መቀስቀስን ተከትሎ ተዋጊ ኃይሎችን ከማደራደር ጋር ተያይዞ ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ የኡሁሩ ኬንያታ ስም በተደጋጋሚ ሲነሳ መቆየቱም ይታወቃል።
የአሁኑ የአሜሪካ እና የኬንያ መሪዎች ውይይት እንደገና የተቀሰቀሰውን ጦርነት ከማርገብና ተፋላሚ ኃይሎቹ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ወደ ድርድር እንዲመጡ ከማድረግ አንጻር የራሱ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ ኬንያ ዓለም አቀፍ ህግን ለማስከበር ላሳየችው ቁርጠኝነት ሩቶን አመስግነዋል፡፡
"የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን ፤ኬንያ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የሩስያን የይስሙላ ሪፈረንደም ውድቅ ያደረገበት የውሳኔ ሃሳብን መደገፏንና የዓለም አቀፍ ህግን ለማስከበር ያሳችውን ቁርጠኝነት ያላቸው አድናቆት ገልጸውላቸዋል” ብለዋል ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ።