አሜሪካ ቲክቶክን ጨምሮ በሌሎች የቻይና ኩባንያዎች ላይ እገዳ ልትጥል እንደምትችል ተገለጸ
የአሜሪካ ኮንግረስ እገዳዎቹ ስለሚጣልባቸው የቻይና ኩባንያዎች ጥናት በማድረግ ላይ ነው ተብሏል
እገዳዎቹ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአሜሪካ እንዳይሰሩ ማድረግንም ይጨምራል
አሜሪካ ቲክቶክን ጨምሮ በሌሎች የቻይና ኩባንያዎች ላይ እገዳ ልትጥል እንደምትችል ተገለጸ።
ሁለቱ የዓለማችን ባለ ብዙ ሀገራት አሜሪካ እና ቻይና የማይግባቡባቸው አጀንዳዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል።
ሁለቱ ሀገራት በተለይም በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአስተዳድር ጊዜ ከቻይና ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ወደ ሀገራቸው በሚገቡ ምርቶች ላይ እገዳዎችን ሲጥሉ ነበር።
በታይዋን ጉዳይ እንደ አዲስ መካረር ውስጥ የገቡት ቻይና እና አሜሪካ አሁን ደግሞ ከምርት እገዳ ወደ ተቋማት እገዳ እየገቡ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
አሜሪካ በተለይም በፍጥነት እያደጉ የመጡ የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ስጋት ላይ የጣሏት ሲሆን ቲክቶክ ደግሞ ዋነኛው ነው።አሜሪካ አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመልቀቅ ተወዳጅ የሆነው የቻይናው ቲክቶክ በአሜሪካ እገዳ ሊጣልበት እንደሚችል ዘገባው ጠቅሷል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ቲክቶክን ለአሜሪካ ኩባንያዎች ካልሸጠች እገዳ እንጥላለን ማለታቸው ይታወሳል።የአሁኑ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድርም ቲክቶክ ኩባንያን ጨምሮ ሎሎች የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአሜሪካ እንዳይሰሩ እገዳ እንደሚጥል ተገልጿል።
እገዳው የሚጣልባቸው የቻይና ኩባንያዎች ማንነት፣ የእገዳው መጠን እና አይነትን በሚመለከት ኋይት ኃውስ መንግስት እና የአሜሪካ ኮንግረስ በውይይት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።
አሜሪካ ከአንድ ሳምንት በፊት መነሻቸውን ከቻይና ያደረጉ 44 በረራዎች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ እገዳ መጣሏ ይታወሳል።