የዊ ቻት አገልግሎቶች ከእሁድ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ይታገዳሉ
አሜሪካ ቲክቶክና ዊቻት መተግበሪያዎችን ልታግድ ነው
ከፊታችን እሁድ ጀምሮ የቻይናዎቹን የቲክቶክና ዊ ቻት መተግበሪያዎችን እንደሚያግድ የአሜሪካ የንግድ ክፍል (Department of Commerce) አስታወቀ፡፡
ክፍሉ መተግበሪያዎቹ ከማከማቻዎች (Stores) እንዳይወርዱ ጭምር እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ሆኖም የቲክቶች መሰረታዊ አገልግሎቶች በእለቱ ሙሉ በሙሉ አይቆሙም ተብሏል፡፡ ለተወሰኑ ሳምንታት እንደሚዘልቁም ነው ክፍሉ የገለጸው፡፡
ሲኤንኤን እስከ ወርሃ ህዳር መባቻ ድረስ በአገልግሎት ላይ ይቆያል ብሏል፡፡
የዊ ቻት አገልግሎቶች ግን ከእሁድ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ይቆማሉ እንደ ክፍሉ የፕሬስ መግለጫ፡፡
መተግበሪያዎቹ የደህንነት ስጋትን ደቅነዋል በሚል እንዲታገዱ አለበለዚያም ለአሜሪካ የቴክኖሎጂ ተቋማት እንዲሸጡ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መታዘዙ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም መሰረት ቲክቶክ ኦራክል ከተሰኘው ግዙፍ የአሜሪካ ተቋም ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ ስለሚችልበት ሁኔታ እየመከረ ነው እንደ ኤንቢሲ ዘገባ፡፡
የንግድ ዋና ጸሃፊዋ ዊልበር ሮስ በሰጡት የጽሁፍ መግለጫ ፕሬዝዳንቱ በቻይው ኮሙኒስት ፓርቲ ከሚቃጡ ጥቃቶች ህዝባቸውንና ሃገራቸውን ለመጠበቅ የትኛውንም ዓይነት ስራ እንደሚሰሩ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ቻይና የአሜሪካ ዜጎችን መረጃዎች ለመመዝበር የምታደርገውን ጥረት ለመግታት ፕሬዝዳንቱ በሰጡት አቅጣጫ በመታገዝ እርምጃ ወስደናልም ነው ዋና ጸሃፊዋ ያሉት፡፡