ጣልያናዊቷ ጠፈርተኛ ክሪስቶፈሬቲ በጠፈር የተዘጋጁ የቲክቶክ ቪዲዮዎች በመልቀቅ ታሪክ ሰርታለች
ሳማንታ ክሪስቶፈሬቲ ትባላለች፡፡ ጠፈር ላይ ካለማቋረጥ ረዥም ርቀት የተጓዘች ጣልያናዊት ጠፈርተኛ በመባል ታሪክ የሰራች ድንቅ እንስት ናት፡፡
ታሪክ መስራት የማይታክታት ክሪስቶፈሬቲ አሁን ላይ ደግሞ አዲስ ታሪክ በመስራት ብቅ ብላለች፡፡
አዲሱ ታሪክ ደግሞ፤ በዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ (International space station) ውስጥ የተዘጋጀ የመጀመሪያው የቲክቶክ ቪዲዮዎች የለቀቀች ጠፈርተኛ መሆኗ ነው፡፡
ክሪስቶፈሬቲ የለቀቀቻቸው ቪዲዮዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየተቀባበሏቸው ይገኛሉ፡፡
ይህች በታሪክ የመጀመሪያ የሆነችው ጣልያናዊት ጠፈርተኛ፤ የቲክቶክ ደረጃና እውቅና እጅጉን ከፍ ማድረጓም ነው እየተነገረላት ያለው፡፡
ክሪስቶፈሬቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር የተጓዘችው እንደፈረንጆቹ 2014 ነበር፡፡ በወቅቱ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ 199 ቀናት በመቆየቷ “በጠፈር በመቆየት ረዥሙን ጊዜ ያስመዘገበች ጠፈርተኛ” ተብላ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጅ የክሪስቶፈሬቲ ክብረወሰን የቆየው እንደፈረንጆቹ እስከ 2017 ብቻ ነበር፡፡ ከክሪስቶፈሬቲ በኋላ ፐጊ ዊትሰን (2017) እና ክሪስቲና ኮች (2019) የተባሉ ጠፈርተኞች የተሻለ ታሪክ ማስመዝገብ ችለዋል፡፡
ክሪስቶፈሬቲ ባሳለፍነው ወርሃ ሚያዝያ 2022 ወደ ምድር የተመለሰች ቢሆንም አሁንም ድረስ የምትለቃቸው የቲክቶክ ቪዲዮዎች ግን በጠፈር ሳለች ያዘጋጀቻቸው ናቸው ፡፡
በተለይም “ዚ ሂችሃይከርስ ጋይድ ቱ ዚ ጋላክሲ” ፊልም ደራሲ የሆነውን ዳግላስ አዳምስ ለማስታወስ የለቀቀችው አንድ ለየት ያለ የቲክቶክ ቪዲዮ አስካሁን 17 ሚልዮን ሰዎች እንደመለከቱት መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
ሌላው ጠፈርተኞች ከምድር ተነስተው ጠፈር ላይ እስኪደርሱ ያለውን ሂደት የሚያስመለክተው የቲክቶክ ቪዲዮም እንዲሁ እስካሁን 1 ነጥብ 2 ሚልዮን ጊዜ መታየቱን ፕሬስ ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡