ሩሲያ ለዩክሬን ሲዋጉ ተይዘዋል ያለቻቸውን የ72 አመት አሜሪካዊ በእስር ቀጣች
የሩሲያ ፍርድቤት ቅጥረኛ ወታደር ሲል የገለጻቸውን ስቴፈን ሁባርድ በስድስት አመት ከ10 ወር እስራት እንዲቀጡ ወስኗል
አሜሪካ ዜጋዋ ተገቢው ህጋዊ ድጋፍ እንዲደረግለት ሞስኮ አልፈቀደችም ስልት ከሳለች
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ሲሳተፉ ተይዘዋል ያለቻቸውን አሜሪካዊ አዛውንት በእስራት ቀጣች።
የ72 አመቱ ስቴፈን ሁባርድ ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት እንደጀመረች ወደ ኬቭ ቅጥረኛ ወታደር ሆነው ለመዝመት መመዝገባቸው ተገልጿል።
ጦርነቱ ከተጀመረ (የካቲት 2022) ከሁለት ወራት በኋላም ከዩክሬን ጦር ጋር ጎን ተሰልፈው ሲጓዙ በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው የተባለው።
የሩሲያ ፍርድቤት በትናንትናው እለት በዋለው ችሎትም የ72 አመቱን አዛውንት በስድስት አመት ከ10 ወራት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የሚቺጋን ነዋሪው ሁባርድ በዩክሬን ጦርነት በቅጥረኛ ወታደርነት ሲሳተፉ ተማርከው በእስራት የተቀጡ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ሆነዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር፥ ሩሲያ ሁባርድ ህጋዊ ድጋፍ እንዲያገኙ አልፈቀደችም ሲሉ ወቅሰዋል።
የእስራት ቅጣት የተላለፈባቸውን ዜጋቸውን ጉዳት በቅርበት ለመከታተል የሚደረገው ጥረት ግን እንደማይቋረጥ ነው ያነሱት።
አሜሪካዊው የ72 አመት አዛውንት የቀረበባቸው ክስ እስከ 15 አመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጣቸው ነበር ተብሏል።
ይሁን እንጂ የእድሜያቸው መግፋት ቅጣቱ እንዲቀንስላቸው ማድረጉን ጉዳዩን የያዙ የህግ ባለሙያዎችን በመጥቀስ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሞስኮ በቁጥጥር ስር የምታውላቸው የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
ይህም በአሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት በቁጥጥር ስር የሚገኙ ዜጎቿን ለማስመለስ እንደ ዋነኛ መደራደሪያ ሊያገለግላት እንደሚችል ነው የተገለጸው።
በተያያዘም በትናንትናው እለት በሩሲያዋ ቮሮኔዝ ከተማ በእስር ላይ የሚገኘው አሜሪካዊ ሮበርት ጊልማን የጸጥታ ሀይሎችን በመሳደብ ተከሶ የሰባት አመት ከአንድ ወር እስር ቅጣት እንደተላለፈበት ተዘግቧል።
በ2022 የመንገደኞች ባቡርን በመመረዝና መንገደኞችን በመረበሽ ክስ በቁጥጥር ስር የዋለው ጊልማን የ3 አመት ከስድስት ወር እስራት ላይ እያለ የጸጥታ ሃይሎችን መሳደቡ ተጨማሪ ቅጣት እንዲተላለፍበት ማድረጉንም ነው የሩሲያው አርአይኤ ኖቮስቲ ዘገባ ያሳየው።
አሜሪካ እና ሩሲያ ባለፈው ነሃሴ ወር 24 እስረኞችን መለዋወጣቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ከተለቀቁት ውስጥም በሩሲያ በእስር ላይ የነበረው የወልስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ዘጋቢው ኢቫን ጄርሽኮቪች ይገኝበታል።