የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ ባይናገሩም የሩሲያ ሚዲያዎ የምዕራባውያን ጥቃት ኢላማ ከሆኑ ቆይተዋል ብለዋል
የሩሲያ የመንግስት ሚዲያዎች የሳይበር ጥቃት እንደደረሰባቸው ተዘገበ።
የሀገሪቱን ዋና ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የሚያስተዳድረው እና የሚቆጣጠረው ቪጂቲአርኬ የተባለው የሩሲያ መንግስት ኩባንያ ሰኞ እለት የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ጥቃቱን ያደረሱት የኪቭ መረጃ መንታፊዎች ናቸው።
የሩሲያ የመንግስት ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ብሮድካስቲንግ ኩባንያ (ቪጂቲአርኬ) ድረገጽ በዛሬው እለት ጠዋት መሰራት ማቅሙን እና በስሩ ያለው ሮሲያ-24 የተባለው የ24 ሰአት የዜና ቻናል ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ እንደነበር ተገልጿል።
ሮይተርስ ቻናሉን ለማግኘት ሲሞክር "503 አገልግሎት የለም።ይህ ጥያቄ የሚያስተናግድ ሰርቨር የለም" የሚል መልእክት ማንበቡን ዘግቧል።
የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮብ "የመንግስት ሚዲያችን የዲጂታል መሰረተልማት ያልተጠበቀ የሳይበር ጥቃት አጋጥሞታል" ብለዋል። ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ቪጂቲአርኬ በሳይበር ጥቃቱ ለደረሰውን ጉዳት መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ ነው።
"ባለሙያዎች ሁኔታውን ለማወቅ እና የተቀናጀ ጥቃት ያደረሱትን ሰዎች ዱካ ለማግኘት እየሰሩ ናቸው"። በበርካታ ቻናሎቹ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ለሩሲያውያን ዜና የሚያቀርበው ቪጂቲአርኬ በዛሬው እለት የሳይበር ጥቃት እንዳጋጠመው አስታውቋል።
የፕሬዝደንት ፑቲን 72ኛ አመት የልደት በአል ጋር ለገጠመው የሳይበር ጥቃት የዩክሬን መረጃ ጠላፊዎች ኃላፊነት መውሰዳቸውን ሮይተርስ የዩክሬን መንግስት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
"የዩክሬን መረጃ ጠላፋዎች በሩሲያ መንግስት ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ላይ መጠነሰፊ ጥቃት በመክፈት 72ኛ አመት እያከበሩ ያሉትን ፑቲን 'እንኳን ደስያለህ'" ማለታቸውን ሲል ዘገባው አክሏል።
ጋዜጣ.ሩ የተባለው የሩሲያ ጋዜጣ በስም ያልጠቀሰውን ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው ጥቃቱ የሬዲዮ ጣቢያዎችን እና በርካታ ክልላዊ ቴሌቪዥኖችን በሚቆጣጠረው ቪጂቲአርኬ የኦንላይን እና የውስጥ አገልግሎቶች ላይ ያነጣጠረ ነበር።
"የኦንላይን እና የውስጥ አገልግሎቶቹ ተቋርጠው ነበር፣ ኢንተርኔትም አይሰራም ነበር። ለማስተካከል ረጅም ጊዜ ይፈጃል" ብለዋል ጋዜጣው ያናገራቸው ምንጭ።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ ባይናገሩም የሩሲያ ሚዲያዎ የምዕራባውያን ጥቃት ኢላማ ከሆኑ ቆይተዋል ብለዋል።
ዛካሮቫ እንዳሉት ይህ ጥቃት "የቅይጥ ጦርነት" አካል ነው።